ለሀገር የተከፈለ ሰማዕትነት!

56

ባሕር ዳር: የካቲት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጣሊያን በ1879 ዓ.ም ዶጋሌ ላይ የካቲት 23/1888 ዓ.ም ደግሞ አድዋ ላይ ሽንፈትን ተከናንባለች። በተለይም ደግሞ የጣሊያን አድዋ ላይ መሸነፍ ያበሳጫቸው እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን በ1898 ዓ.ም ለንደን ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ሥር እንድተዳደር ወሰኑ።

ጣሊያንም በ1928 ዓ.ም ያለ የሌለ ኃይሏን አሰልፋ ኢትዮጵያን ድጋሜ ወረረች። በመሬት በታንክ፣ በመድፍ እና በመትረየስ፣ በአየር ቦምብ በሚጥሉ እና የመርዝ ጋዝ በሚተፉ አውሮፕላኖች የኢትዮጵያን ሕዝብ ጨፈጨፈች፡፡ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ላለማስደፈር ጠላትን በሰይፍ እና በጎራዴ ጭምር ተፋለሙ። ይሁን እንጅ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀው የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር ሚያዝያ 27/1928 ዓ.ም እስከ አዲስ አበባ መዝለቅ ቻለ።

ጣሊያን እስከ አዲስ አበባ ድረስ መዝለቅ ቢችልም ግን ኢትዮጵያውያን በዱር በገደሉ እንዲሁም በዋና ዋና ከተሞች በጠላት ላይ ጥቃት መሰንዘር ቀጠሉ። ከተሰነዘሩት ጥቃቶች መካከል ደግሞ በግራዚያኒ ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ተጠቃሽ ነው። ድርጊቱ የተፈጸመው ደግሞ የካቲት 12/1929 ዓ.ም ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ስለጣሊያን ንጉሥ ቪክቶር ኢማኑኤል ልጅ መውለድ ደስታ ለማብሰር በገነት ልዑል ቤተ መንግሥት አዳራሽ ሹማምንቱን እና ሕዝቡን በሠበሠበበት ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ አብርሃም ደቦጭ፣ ሞገስ አስግዶም እና ሌሎች ወጣቶች ቦንብ ይዘው ወደ ሥብሠባው ገቡ፡፡

ወጣቶቹ ወደ አዳራሹ እንደገቡ ግራዚያኒ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ፣ አርበኞች እና ንጉሡ በንቀት ይናገራል፡፡ ወጣቶቹ በግራዚያኒ የንቀት ንግግር እና በሥብሠባው ውስጥ በታደመው ተሠብሣቢ በመናደዳቸው ወደ ግራዚያኒ ቀስ ብለው በመጠጋት ሰባት ቦንቦችን በተከታታይ ወረወሩ፡፡ ተሠብሣቢው በመጀመሪያው ቦንብ ፍንዳታ የደስታ ርችት መስሎት አልተደናገጠም፡፡ በሁለተኛው የቦንብ ፍንዳታ ግራዚያኒ ተመትቶ ከብዙ ቦታ ላይ ቆሰለ፤ የጦር ኃይል አዛዥ የነበረውን አውራሊያ ሊአታ ዐይኑ ጠፋ፤ እግሩ ተቆረጠ፡፡ ሌሎች ሹማምንትም ሕይዎታቸው አለፈ።

በቦታው የነበሩት የፋሽስቱ ወታደሮች የቦንብ ፍንዳታው መቆምን እንዳረጋገጡ ከየተደበቁበት በመውጣት በታጠቁት የጦር መሳሪያ በአካባቢው በተገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የጥይት ዶፍ ማዝነብ ጀመሩ። ከሬሣ መካከልም የሚተነፍስ እየፈለጉ ጭምር መግደሉን ቀጠሉ። ወታደሮቹ ከግቢው በመውጣት በከተማው እየተሯሯጡ ሱቆች ሁሉ እንዲዘጉ አደረጉ።

የውጭ ሀገር ሰዎችም ከቤታቸው እንዳይወጡ አዘዙ። በተለይ ፎቶግራፍ ማንሻ እየተፈተሸ ተወሰደ። የፖስታ እና የስልክ አገልግሎት ተቋረጠ። ወዲያውኑ መንገዶች በወንዶች፣ በሴቶች፣ በልጆች ሬሣ ተሞላ። ደም እንደ ውኃ ፈሰሰ። ሰዎች በቤት ውስጥ እንዳሉ በእሳት እንዲቃጠሉ ተደረገ። ቃጠሎው ቶሎ እንዲያያዝም ቤንዚን እና ዘይት ይጠቀሙ ነበር። ሰው እሳቱን እየሸሸ ከቤቱ ሲወጣ በመትረየስ ይገድሉታል።

በዚያን ሌሊት የኢጣሊያ መኰንኖች በሚያማምር አውቶሞቢላቸው ከሚስቶቻቸው ጋር ኾነው ብዙ ከሞተበት እና ብዙ ቃጠሎ ከሚታይበት ቦታ ላይ ቆመው ይሳለቃሉ። ግራዚያኒም ሆስፒታል ውስጥ ኾኖ በመስኮት የከተማዋን መቃጠል እያየ ይስቅ ነበር። ባለጥቁር ሸሚዞች በቤት ውስጥም ኾነ ከሚገድሏቸው ሴቶች አንገት እና ጆሮ ላይ የዘረፉትን ወርቅ በኢጣሊያ ባንክ ያስቀምጣሉ። እያንዳንዱ ጣሊያናዊም ምን ያህል ሰው እንደገደለ በኩራት ይናገራል።

የካቲት 12 ቀን በተጀመረው እልቂት በሦስት ቀን ውስጥ 30 ሺህ ንፁሃን በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተገደሉ። ሌላው እየታፈሰ ወደ ሞቃዲሾ እና ሌሎች የበረሃ እሥር ቤቶች ተላከ። እስር ቤቶች በመጨናነቃቸው የተነሳ ሜዳውን በሽቦ በማጠር እንዲታጎሩ ተደርጓል። ብዙዎችም በሚሰጧቸው የተበላሸ ምግብ እና ውኃ ምክንያት በእስር እንዳሉ ሕይዎታቸው እንዲያልፍ ተደርጓል።

የጀግኖቹ መስዋዕትነት! ወጣቶቹ በጠላት ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ በጓደኛቸው በስምኦን መኪና ከአዲስ አበባ ወደ ፍቼ በማቅናት ከአርበኞች ከእነራስ አበበ ጋር ተቀላቅለው እስከ 1932 ዓ.ም ድረስም ጠላትን ተዋጉ። የጣሊያን መንግሥት የሁለቱን ጀግኖች ፎቶ ግራፍ በየሀገሩ በትኖ እነሱን ይዞ ላመጣ ወይንም የአሉበትን ቦታ ለጠቆመ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚሸለም አሳውቆ ባንዳ እና ቅጥረኛ ሰላዮችን በማሰማራት ከፍተኛ ክትትል ማድረጉን ቀጠለ። ይህንን የተረዱት ጀግኖች ከአርበኞች ጋር በመነጋገር ወደ ሱዳን ሀገር እንዲሄዱ ተወሰነ። ጀግኖቹም መንገድ እያሳበሩ ቋራ እንደ ደረሱ በጠላት እጅ ወደቁ።

እንደተያዙም የጣሊያኑ ሹም በዕለቱ በሞገስ ላይ በስቅላት እንዲቀጣ ወሰነ። በእዚህ ጊዜ ጀግናው አብርሃም የጣሊያኑን ሹም “…የወንድሜን መሞት ቆሜ አላይም፤ መጀመሪያ እኔን ግደለኝ፤ በግራዚያኒ ላይ አደጋ የጣልኩት እኔ ነኝ፤ ለሀገሬ በሠራሁት ሁሉ እኮራለሁ፤ አሁንም ለሀገሬ ስሞት ደስ ይለኛል…” ብሎ እንደ ተናገረ የጣሊያኑ ሹም በጣም ተናዶ ሽጉጡን አውጥቶ ተኮሶ ይገድለዋል።

ይህንን ፋሺስታዊ ድርጊት የተመለከተው ሞገስ አስገዶም «…አንተ ፋሽሺት አሁን የገደልከው የዚች ሀገር ጀግና ልጅ እና ደመላሽ ነበር፤ ብዙ አብርሃሞች በእዚች ጀምበር ተወልደው ያድራሉ፤ አንተም ሆንክ አተላው ታሪክህ አብራችሁ ወደ እዚች ምድር ትገባላችሁ…» ብሎ ሲናገረው አሁንም በንዴት የጦዘው ፋሺስት በሽጉጥ ይገድለዋል። የሁለቱም ሥራዓተ ቀብር በእዚያው በቋራ ከተማ እንደተቀበረ ይነገራል። ነገር ግን ከነፃነት በኋላ አጽማቸው ከተቀበረበት ቦታ ተነስቶ በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ከአርበኞች መቃብር ጋር በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል።

ከ41 ዓመታት በኋላ ተመልሶ ለወረራ የመጣው በማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ የሚመራው የፋሺስት ጦር ከየካቲት 12 ጀምሮ ለሦስት ቀናት ከ30 ሺህ በላይ ሰላማዊ ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፏል፡፡ የተጨፈጨፉ ዜጎችን ለመዘከር የካቲት 12 በብሔራዊ ደረጃ እንዲዘከር በ1934 ዓ.ም ታወጀ፡፡ በ1951 ዓ.ም ደግሞ 6 ኪሎ አካባቢ የሚገኘው እና 28 ሜትር ርዝመት እንዳለው የሚነገረው የሠማዕታት መታሰቢያ ሐውልት እንዲቆም ተደርጓል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article88ኛው የሰማዕታት መታሰቢያ በአዲስ አበባ አየተከበረ ነው።
Next articleከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።