14 ሚሊዮን ማሳ በሁለተኛ ደረጃ ካዳስተር በመመዝገብ ዲጂታላይዝድ መደረጉን መሬት ቢሮ አስታወቀ።

47

ባሕር ዳር: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተራቸውን አስይዘው ከፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያስችል ውይይት በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል። የመሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ቢሮው የገጠር መሬት አሥተዳደር ሥርዓትን እያዘመነ ይገኛል ብለዋል። እንደ ክልል ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑት ባለይዞታዎች 18 ነጥብ 2 ሚሊዮን ማሳዎች አላቸው ነው ያሉት።

በካርታ ደረጃም 14 ሚሊዮን የሚደርሰው ማሳ በሁለተኛ ደረጃ ካዳስተር በመመዝገብ ዲጂታላይዝድ ተደርጓል ብለዋል። 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚደርሱ አርሶ አደሮችም የሁለተኛ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸው ነው አቶ ሲሳይ የተናገሩት። በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች መሬትን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ ተተግብሯል ያሉት አቶ ሲሳይ በቀበሌ እና በአርሶ አደር ደረጃ ደግሞ አፈጻጸሙን ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በገጠር መሬት የይዞታ መረጋገጥ የካዳስተር ሥራ ሽፋኑ 70 በመቶ መድረሱንም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። በ126 ወረዳዎች ዘላቂነት ያለው የገጠር መሬት አሥተዳደር መረጃ ሥርዓት ተገንብቷልም ነው ያሉት። በመኾኑም ከመሬት አገልግሎት እንደ ውርስ፣ ስጦታ፣ ልውውጥ፣ ኪራይ ያሉ ኹነቶች በዘመናዊ መንገድ በሲስተም እየተከናዎኑ እንደሚገኙ ነው ቢሮ ኀላፊው የተናገሩት።

የአርሶ አደሩ ይዞታ በዘመናዊ መንገድ በሲስተም መሰነዱ ደግሞ ማንም ሰው ካላግባብ መሬትን ነጥቆ በኃይል መጠቀም እንዳይችል አድርጓል ያሉት አቶ ሲሳይ የአርሶ አደሩን መብት እና ይዞታ በሚገባ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል። አርሶ አደሩ የመሬቱን የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በዋስትናነት አስይዞም ከአበዳሪ ተቋማት ጋር ብድር መውሰድ መጀመሩን ነው አቶ ሲሳይ የተናገሩት።

መሬት በሥርዓት በመተዳደሩም እንደ ክልል ከመሬት አሥተዳደር ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች፣ ግጭቶች እና ክርክሮች በእጅጉ ቀንሰዋል ብለዋል። ተጋላጭ የኾኑ የኀብረተሰብ ክፍሎች እንደ ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞች የመሬት የይዞታ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።

በመሬት ረገድ የፍትሕ ሥርዓቱም ትክክለኛ ብይን እንዲሰጥ አድርጓል ብለዋል። መሬት በሥርዓት በመተዳደሩም ከእርሻ መሬት የሚገኘው ገቢ ከ50 እስከ 65 በመቶ ጨምሯል ያሉት አቶ ሲሳይ አርሶ አደሩም በዕውነተኛ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ትክክለኛ ግብር እየከፈለ ስለመኾኑ አስረድተዋል።

ክልሉ መልማት የሚችል ሰፊ መሬት እና ማልማት የሚችል እምቅ የከርሰ ምድር እንዲሁም ከፍተኛ የገጸ ምድር ውኃ እንዳለውም ተናግረዋል። አቶ ሲሳይ ወጣቱን አቀናጅቶ መሥራት ከተቻለ ብልጽግና ሩቅ አይኾንም ነው ያሉት። አርሶ አደሩም መሬቱን በዋስትና አስይዞ ከባንኮች እና ከገጠር ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብድር በመውሰድ አካባቢውን በበጎ መቀየር እና የአኗኗር ዘይቤውን ሊያዘምን እንደሚገባም ተናግረዋል።

አቶ ሲሳይ እንደ ክልል እስካሁን ሁለት ባንኮች እና 12 የሚደርሱ ማይክሮ ፋይናንሶች ከ18 ሺህ በላይ ለሚኾኑ አርሶ አደሮች ከ973 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ሰጥተዋል ብለዋል። ብድር የወሰዱ አርሶ አደሮችም ምርታማነትን ለመጨመር የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በቴክኖሎጂ ለማገዝ እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ተናግረዋል። ጅምሩም እንዲጠናከር ይፈለጋል ነው ያሉት።

ከደብረ ብርሃን የሸዋ ብርሃን አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ሥራ አሥኪያጅ ደረጃ ተፈራ አርሶ አደሩን ትኩረት አድርገን እየሠራን እንገኛለን ብለዋል። የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ላላቸው አርሶ አደሮችም ወደ 13 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ማበደራቸውን ተናግረዋል። እስካሁንም የተፈጠረ ችግር የለም ያሉት አቶ ደረጀ አርሶ አደሮችም ብድራቸውን በአግባቡ እየመለሱ ነው ብለዋል።

የጸደይ ባንክ የማይከክሮ እና አነስተኛ ፋይናንስ ምክትል ፕሬዝዳንት አራጌ ጌታሁን እንዳሉት የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቅት ላላቸው አርሶ አደሮች የብድር አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። አርሶ አደሮችም በሚወስዱት ገንዘብ ግብርናን በቴክኖሎጂ ተጠቅመው ምርታማ እንዲኾኑ እያደረጋቸው ነው።

የአኮፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አብርሃም ወዳጆ “ተቋማችን ለአርሶ አደሮች 90 ሚሊዮን ብር ተደራሽ አድርጓል፤ ወደፊትም ሰፋፊ ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleግብርን በታማኝነት በመክፈል ሀገራዊ ግዴታን መዋጣት እንደሚገባ የደብረታቦር ከተማ ግብር ከፋዮች ተናገሩ።
Next articleያለውን የመልማት እድል በአግባቡ ለመጠቀም ሰላም ያስፈልጋል።