
ደብረ ታቦር: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሀገራችን፣ ፍቅር ለሕዝባችን፣ ግብር ለሁለንተናችን” በሚል መልዕክት በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የግብር ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል። በንቅናቄ መድረኩ ስፖርታዊ ሁነቶችን ጨምሮ ለምሥጉን ግብር ከፋዮች የምስክር ወረቀት እና ሽልማት ተበርክቷል።
ከተሸላሚዎች መካከል እጹብ ጌጡ ግብር መክፈል ለአንድ ሀገር የዕድገት መሠረት መኾኑን ተናግረዋል። “ለምንሠራው ሥራ ታማኝ በመኾን ደረሰኝ በመቁረጥ ሀገራዊ ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል” ብለዋል። ሌላው ምሥጉን ግብር ከፋይ ታዘባቸው እጅጉ ግብርን በወቅቱ እንደሚከፍሉ ተናግረዋል። የንግዱ ማኅበረሰብ ግብርን በታማኝነት በመክፈል ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት ግብር ከፋዮች ግብር መክፍል ለአንድ ሀገር ዕድገት ዋልታ መኾኑን ተናግረዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ጌታሰው አምሳሉ ግብርን ለመሰብሰብ ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። የሀገርን ዕድገት ለማስቀጠል ግብር በወቅቱ መሰብሰብ እንዳለበት ገልጸዋል። ሕገ ወጥ ንግድ እና መሰል አላስፈላጊ ድርጊቶችን በጋራ በመቃወም መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን አንድ ከተማ ሊለማና ሊያድግ የሚችለው በሚሰበሰብ ግብር በመኾኑ ግብርን በተገቢው መንገድ መሰብሰብ ያስፈልጋል ብለዋል። ከተማዋ የቱሪዝም ማዕከል እና ትልልቅ ስብሰባዎች የሚካሄድባት መኾኗን አንስተዋል። ለሁሉም መሠረቱ ሰላም ነው ያሉት ከንቲባው ለሰላም ሁላችንም ልንሠራ ይገባል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን