
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) የተከዜ ዓሳን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ እየተሠራ ነው። በ16 ሚሊዮን ብር ወጭ የተከዜን ዓሳ ሀብት ሳይበላሽ ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎች ለአራት ወረዳዎች ተሰጥዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ጎንደር ዞን ለሚገኙ አራት ወረዳዎች ማለትም ስሃላ ሰየምት፣ ዝቋላ፣ አበርገሌ እና ጠለምት ወረዳዎች ለአካባቢዎቹ ተስማሚ የሆኑና ማቀዝቀዥ ያላቸው አራት ተሽከርካሪዎች ዛሬ ሚያዝያ 29/2012 ዓ.ም ተሰጥቷቸዋል።
ተሽከርካሪዎችን ያስረከቡት የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ደበበ ዓድማሱ ተሽከርካሪዎቹ ወደ ሥራ መግባታቸው በስፋት ይነሳ የነበረውን የዓሳ ሀብት የገበያ ትስስር ችግር እንደሚቀርፉ ተናግረዋል።
ተሽከርካሪዎቹ እያንዳንዳቸው በአንድ ጊዜ 60 ኩንታል ወደ ማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ የሚችሉ ናቸውም ብለዋል።
ከተሸከርካሪዎቹ በተጨማሪም በሰቆጣና ነይረአቚ ከተሞች ላይ የተገነቡትን የዓሳ መሸጫና ማከፋፈያ ሼዶች ሥራ ለማስጀመር ርክክብ እየፈፀሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአበርገሌና የጠለምት የዓሳ መበለቻ ሼዶችም ጀነሬተርና ውኃ ማጠራቀሚያ በርሚሎች በመገጠማቸው ሥራ መጀመር እንደሚችሉ ተመላክቷል፤ የዝቋላው ግን ለዓሳው ቅርበት ያለው ቦታ ላይ ያልተሠራ እና የመንገድ ቅየሳ ችግርም ያለበት መሆኑ ነው የተገለጸው።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ በሪሁን ኪዳነማሪያም ተሽከርካሪዎችን በመረከባቸው ወደ ገበያ ለማቅረብ ይፈጠር የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ ዓሳን በጥራትና በትኩስነቱ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ተሽከርካሪዎቹ በሚሠሩባቸው ቦታዎች ያሉ የመንገድ ችግሮችን የክልሉ መንግሥት እንዲፈታ ማሳወቃቸውንም ገልጸዋል።
የክልሉ ርእሰ መሥተዳደር ተመሥገን ጥሩነህ ከቅዳሚት እስከ ተከዜ ያለውን መንገድ በ2013 ዓ.ም የክልሉ መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራቸው ፕሮጀክትቶች አንዱ መሆኑን ቀደም ብለው ለአብመድ መናገራቸው ይታወሳል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወርቁ ለምለሙ ደግሞ ለጠለምት ወረዳ የተደረገው ድጋፍ ሰፊ የገበያ ዕድልን የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ወረዳው ዝናብ አጠር በመሆኑ የዓሳ ዘርፉ ለአካባቢው ዓይነተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ይሆናልም ብለዋል።
የተከዜ ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ከ90 ከመቶ በላዩ አማራ ክልል ላይ ቢገኝም በልዩ ልዩ መሠረተ ልማቶች መጓደል ምክንያት የገበያ ትስስር ሳይፈጠርና የአካባቢዎቹ ወጣቶ ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አብመድ በተደጋጋሚ ሲዘግብ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡
ዘጋቢ:- ግርማ ተጫነ