“በአረርቲ ከተማ የተመረቀው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)

44

ደብረ ብርሃን: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን በአረርቲ ከተማ በ117 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተመርቋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ ምንጃር ሸንኮራን ጨምሮ በዞኑ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጭ የውኃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ ችሮታው ሹመት በአረርቲ ከተማ የተገነባው የውኃ ፕሮጀክት የከተማውን የመጠጥ ውኃ ተደራሽነት ከ33 በመቶ ወደ 87 በመቶ ከፍ አድርጎታል ብለዋል። ይህ ፕሮጀክት ከ63 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋልም ነው ያሉት።

በከተማው የነበረው የንጹህ መጠጥ ውኃ እጥረት ነዋሪውን ለችግር ዳርጎት መቆየቱን የተናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ፕሮጀክቱ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ችግሩን እንደፈታላቸው ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በክልሉ 500ሺህ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የውኃ ፕሮጀክት በተያዘው በጀት ዓመት ለማስመረቅ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የተመረቀው የአረርቲ የመጠጥ የውኃ ፕሮጀክት ከዚህ ውስጥ አንዱ መኾኑን አንስተዋል። እስካሁን በካፒታል በጀት፣ በብድር እና በፕሮጀክቶች እገዛ ሢሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል። አሁን ግን በራስ አቅም ለመገንባት በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የአረርቲ ከተማ ሕዝብ ለዚህ መልካም ጅማሮ አሳይቷል ብለዋል፡፡ የተሠራውን ፕሮጀክት ማጠናከር እና መጠበቅም ይገባል ነው ያሉት።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) የተመረቀው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደረሰኝ አጠቃቀም እና ሕጋዊ ተጠያቂነቱ!
Next articleሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ እና የዕዙ መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ጎበኙ።