የደረሰኝ አጠቃቀም እና ሕጋዊ ተጠያቂነቱ!

138

ባሕር ዳር: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደረሰኝን መቀበል እና መስጠት ላይ ክፍተቶች ሲስተዋሉ ይታያል። በርካታ ሰዎች ደረሰኝ መጠየቅ ሥልጡንነት መኾኑንም አይገነዘቡም። አንድ ሰው ላገኘው አገልግሎት ደረሰኝ መጠየቁ ሀገሩን ለማልማት በሚደረግ ጥረት አንድ ጠጠር የመወርወር ያክል እንደኾነስ ምን ያህሎቻችን እንገነዘብ ይኾን?

ለመኾኑ ደረሰኝ ምንድን ነው? ደረሠኝ በዕቃ ወይም በአገልግሎት ግብይት ላይ ተመስርቶ ከሻጩ ለገዥው የሚሠጥ እና ግብይት ስለመፈጸሙ፣ ገንዘብ ስለመሠብሠቡ፣ ዋጋው ስለመከፈሉ ወይም ለወደፊት ለመክፈል ውል ስለመገባቱ የሚያሳይ ሰነድ ነው ይላሉ በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ የኾኑት ደመቀ ይብሬ፡፡

በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 መሠረት ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በስተቀር የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች ደረሰኞችን የመያዝ ግዴታ ተጥሎባቸዋልም ይላሉ የሕግ ባለሙያው፡፡ የደረጃ “ሀ” እና የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የንግድ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ግብይቱ በደረሰኝ እንዲደገፍ ማድረግ እንዳለባቸው ይደነግጋል ብለዋል፡፡

አንድ ደረሰኝ ሕጋዊ የሚያሰኘው ምን ሲይዝ ይኾን? እንደ ሕግ ባለሙያው ማብራሪያ አንድ ደረሰኝ ሕጋዊ የሚኾነው መያዝ ያለበትን ዝርዝር ጉዳይ ሲይዝ እንደኾነ አስገንዝበዋል። በሽያጭ ደረሰኝ መመሪያው አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት መያዝ ያለበትን ዝርዝር ጉዳይ ሲያብራሩ፦ የአቅራቢው ሙሉ ስም፣ አድራሻ እና የተመዘገበ የንግድ ስም የታተመበት መኾን ይኖርበታል።

የአቅራቢው የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ቁጥር እና ለታክስ የተመዘገበበት ቀን የታተመበት፤ የደረሰኙ ተከታታይ ቁጥር የታተመበት እንዲኾን ይጠበቃል ነው ያሉት። ደረሰኙ ላይ የገዥው ሙሉ ስም፣ አድራሻ እና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፤ የተጓጓዘው፣ የተሰጠው አገልግሎት ዓይነት እና መጠን፤ ታክስ የሚከፈልበት ግብይት ላይ የሚፈለገውን የተጨማሪ እሴት ታክስ መጠን፤ በፊደል እና በአሃዝ የተጻፈ ጠቅላላ የሽያጭ ዋጋ መያዝ አለበት ይላሉ።

ደረሰኙ የተሰጠበት ቀን፤ ደረሰኙን ያዘጋጅው እና ገንዘቡን የተቀበለው ሠራተኛ ሥም እና ፊርማ፣ የደረሰኝ አታሚው ድርጅት ስም፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣ የታተመበት ቀን እና የአታሚው የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ቁጥር፤ ደረሰኙ እንዲታተም በኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተፈቀደበት ደብዳቤ ቁጥር እና ቀን መያዝ እንዳለበት የሕግ ባለሙያው አብራርተዋል።

ደረሰኝ አለመሥጠት የሚያስከትለው ተጠያቂነት ምንድን ነው? የገቢዎች ቢሮ የግብር አወሳሰን አሰባሰብ እና ክትትል የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አትንኩት በላይ ደረሰኝ ተጠቃሚው ግብር ከፋይ ኀላፊነቶች እንዳሉበት ተናግረዋል። በመመሪያው አንቀጽ 19 ላይ ማንኛውም በኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዕውቅና ያለውን ደረሰኝ የሚጠቀም ግብር ከፋይ ኀላፊነቶች እንዳሉበትም አስገንዝበዋል።

በባለሥልጣኑ ፈቃድ እና ዕውቅና ያልተሰጣቸውን ደረሰኞች አለመጠቀም እንደሚገባ አስረድተዋል። ለአንድ ግብይት ጥቅም ላይ የዋለን ደረሰኝ ለሌላ ግብይት አለመጠቀም ይገባልም ብለዋል። በበራሪ እና ቀሪ ቅጠሎች ላይ የተለያየ መረጃ አለመመዝገብ ብሎም ግብይቱ ከተከናወነበት ሽያጭ ዋጋ የተለየ የገንዘብ መጠን በደረሰኙ ላይ አለማስፈር እንደሚጠይቅም አስገንዝበዋል።

የደረሰኝ ህትመት ከተፈቀደለት ግብር ከፋይ ውጭ ለሌላ ግብር ከፋይ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ተገቢ እንዳልኾነም አብራርተዋል። ያለደረሰኝ ሽያጭ ማከናወን ያስጠይቃል ያሉት ዳይሬክተሩ ደረሰኝ ለሚጠይቁ ግዥ ፈጻሚዎች ሽያጭ አለመከልከል፤ ለአንድ አይነት ተግባር የሚውል ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ደረሰኝ በማሳተም ጥቅም ላይ አለማዋል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በበራሪ እና ቀሪ ቅጠሎች ያለውን ደረሰኝ ማሳተም፣ ደረሰኞችን በጥንቃቄ መያዝ እና ግብይት የተፈጸመባቸውን ደረሰኞች በጥንቃቄ መያዝ እና ግብይት የተፈጸመባቸውን ደረሰኞች በግብር ወይም በታክስ ሕጉ እስከተገለጸ ጊዜ ድረስ ይዞ መቆየት፣ ለሒሳብ ምርመራ ወይም ለግብር አወሳሰን እንዲቀርብ በሚጠየቅበት ጊዜ ማቅረብ እንደሚገባም አብራርተዋል።

የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያው በተለያየ ምክንያት አገልግሎት መስጠት ሳይችል ሲቀር በባለሥልጣኑ ፈቃድ እና ዕውቅና የታተመ የሽያጭ ደረሰኝ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ግብይት ተከናውኖ ለግዥ ደረሰኝ አንደተሰጠ ሁለተኛውን ቅጂ ወዲያውኑ ለሒሳብ ክፍል ማስተላለፍ እና ከማመሳከሪያ ሰነዶች ጋር የማያያዝ ሥራ መሠራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ደረሰኝ ያሳተመ ግብር ከፋይ በተለያየ አካባቢ ወይም በተለያየ የንግድ ዘርፍ ሲጠቀም የደረሰኝ ቅደም ተከተልን ተፈፃሚ ሊያደርግ ይገባልም ነው ያሉት። ይህ ሳይኾን ከቀረ ግን እንደተፈጸመው የጥፋት መጠን ታይቶ አሥተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃዎችን ሊያሰጥ ይችላል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ: ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቆቦ ጊራና መስኖ ልማት ኘሮጀክትን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው።
Next article“በአረርቲ ከተማ የተመረቀው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)