
ወልድያ: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ኘሮግራም ጽሕፈት ቤትን እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል። በራያ ቆቦ ወረዳ አራዱም 08 ቀበሌ የኩታገጠም የሐብሐብ ቡቃያ ማሳን እና በቆቦ ከተማ አሥተዳደር የኩታገጠም ማንጎ ልማት ማሳን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጎብኝተዋል።
የቆቦ ጊራና መስኖ ልማት ኘሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ መንገሻ አሸብር በ65 ኘሮጀክቶች ሁለት ሺህ 880 ሄክታር በላይ መሬት እየለማ መኾኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ 8ሺህ 141 አባወራ እና 43 ሺህ 912 ቤተሰብን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተብራራው። ይሁን እንጂ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ስለደረሰበት በሙሉ አቅም መሥራት አልተቻለም ነው ያሉት።
በኘሮጀክቱ 202 ጉድጓድ ተቆፍሮ ታሽጎ ተቀምጧል ብለዋል። ሁሉንም ጉድጓድ ሥራ ለማስወጀመር 263 ሜጋ ዋት በላይ ኀይል እንደሚያስፈልግ ኀላፊው አስረድተዋል። ኘሮጀክቱ ታቅዶ ሲጀመር በ1ሺህ 740 የከርሰምድር ጉድጓድ ምንጃር ሸንኮራን ጨምሮ እስከ አዋሽ ተፋሰስ 73 ሺህ 70 ሄክታር ማልማት እንደሚቻል በጥናት መረጋገጡን ኀላፊው ነግረውናል።
አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ከሰሜኑ ጦርነት በፊት የተሻለ ተጠቃሚ እንደነበሩ ገልጸው በጦርነቱ የትራንፈርመር ዝርፊያ በመከሰቱ የኀይል ዝጥረት እና የመብራት መቆራረጥ በማስከተሉ የመስኖ ሥራው ላይ ችግር እንደገጠማቸው ገልጸዋል። የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ(ዶ.ር) የቆቦ ጊራና መስኖ ልማት ኘሮጀክትን ቀሪ 35 ጉድጓድ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት የባለድርሻ አካላትን ድጋፍ የሚያስፈልግ በመኾኑ የሚመለከተው ሁሉ አብሮ አንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል። ኘሮጀክቱ 73 ሺህ ሄክታር ለማልማት ትልቅ ካፒታል የሚጠይቅ በመኾኑም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በትብብር ለመሥራት ጥረት እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!