
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ለእንስሳት ሃብት ልማት የተለዩ የወተት እና የሥጋ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን የያዘ ክልል ነው። የክልሉ እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው የእንስሳት ሃብት በክልሉ ከሰብል ልማት ቀጥሎ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድርሻ ያለው ዘርፍ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ትኩረት ተሰጥቶትም እየተሠራ ይገኛል።
በትኩረት እየተሠራባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አንዱ ነው። በከተማ አሥተዳደሩ ከ700 በላይ አርሶ አደሮች በወተት ሃብት ልማት ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ። በዘርፉ ከተሠማሩ ግለሰቦች ውስጥ ደግሞ አቶ ተስፋሁን ቀናው ይገኙበታል። አቶ ተስፋሁን በወተት ላም እርባታ ዘርፍ ከመሰማራታቸው በፊት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ለ30 ዓመታት ያህል በመንግሥት ሥራ ላይ ቆይተዋል።
ከመንግሥት ሥራ ጎን ለጎን ከአርሶ አደሮች ቦታ በመግዛት የንብ ማነብ ሥራ ጀመሩ። በሂደት ደግሞ የንብ ማነብ ሥራውን ወደ ወተት ልማት ቀየሩት። በመንግሥት ሥራ ከሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዝ በመቆጠብ ነበር 1 የሐበሻ ላም ለቤተሰብ ወተት ፍጆታ በመግዛት ሥራውን የጀመሩት። በሂደት በባለሙያዎች በተደረገላቸው ሙያዊ ድጋፍ የሐበሻዋን ላም ወደ ተሻሻለ ዝርያ ቀየሩ።
አሁን ላይ 40 የሚኾኑ ላሞች፣ ጊደሮች እና ጥጆች እያረቡ ይገኛሉ። በቀን እስከ 200 ሊትር ወተት ለገበያ ያቀርባሉ። በቀን ከ12 ሺህ ብር ያላነሰ ገቢም ያገኛሉ። ከእንስሳት እርባታ እና በእንስሳት ተዋጽኦ ባገኙት ገቢ ሦስት ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት አሥተምረዋል በጎንደር ከተማ የመኖርያ ቤትም ሠርተዋል።
ልጆቻቸውም በዘመናዊ ከብት እርባታ ላይ እንዲሠማሩም አድርገዋል። አሁን ላይ በጎንደር ከተማ ወተት በብዛት እና በጥራት እያቀረቡ ይገኛሉ። ለአምስት ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። በቀጣይ ዘርፉን ለማስፋትም አቅደዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእርባታ ባለሙያ ሙሌ ዓለሙ እንዳሉት በከተማ አሥተዳደሩ ዶሮ እርባታ፣ ንብ ማነብ፣ በግ፣ ፍየል እና ዳልጋ ከብት ማድለብ እና የወተት ሃብት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
ከተማ አሥተዳደሩ አሁን ላይ 754 አባላትን የያዙ 6 ማኅበራት በወተት ሃብት ልማት ተሠማርተው ይገኛሉ። በቀን በአማካይ 10 ሺህ ሊትር ወተት ያመርታሉ። ለከተማው ማኅበረሰብም እያቀረቡ ይገኛሉ። አልፎ አልፎ የሚታየውን የገበያ ችግር ለመፍታትም ግለሰቦች ከተለያዩ ድርጅቶች ባገኙት ድጋፍ የማቀነባበር ሥራ እየሠሩ ነው። ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚመለከታቸው ተቋማት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!