የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ቴክኖሎጅን በመጠቀም አገልገሎቱን ለማሻሻል እንደሚሠራ አስታወቀ።

22

ባሕር ዳር: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን እና የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ የለማ ሶፍትዌርን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል የውል ሥምምነት ተፈራርመዋል። የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የሚጠቀሙበት ሶፍትዌሮችን በማበልጸግ ሥራ ላይ ይገኛል። ከክልሉ አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ቢሮው ሶፍትዌርን አበልጽጎ ለባለሥልጣኑ አስረክቧል።

የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኀላፊ አቤል ፈለቀ የባለሥልጣኑን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ለአጠቃቀም ቀላል የኾነ ቴክኖሎጅን ማበልጸግ እንደተቻለ ተናግረዋል። ቴክኖሎጅው የባለሥልጣኑን የአገልግሎት ጥራት እና ፍጥነት ለማሻሻል እንደሚያግዝም አስረድተዋል። የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ እንደ ክልል ለቴክኖሎጂ ሽግግር የተሰጠውን ትኩረት እንደሚያደንቁ ገልጸዋል። እርሳቸው የሚመሩት ባለሥልጣንም የለማ ሶፍትዌርን በመጠቀም የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ስለመኾናቸው ተናግረዋል። የቴክኖሎጂ ልምምድ በማድረግ አሠራሮችን ማዘመን የግድ እንደሚል አውስተዋል።

የለማው ሶፍትዌር ውስብስብ የአሠራር ችግሮችን በመፍታት የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ እንደሚያግዝም ተስፋ አድርገውበታል። ሶፍትዌሩ በሠራተኞች እና አሠራሮች ዘንድ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለመሙላት፣ ብልሽቶችን ለመቆጣጠር እና ለማስተካከል ያስችላልም ነው ያሉት።

በርክክቡ የተገኙት የግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና ውኃ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከፍያለው ሙላቴ ለውጡን በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ መደገፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ስለመኾኑ አንስተዋል። ተቋማት በትብብር መሥራታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ሁለቱ ተቋማት የለማውን ሶፍትዌር ርክክብ እና ወደፊት አብሮ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሥምምነትም ተፈራርመዋል።

የአሚኮየአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን መንግሥት አመሰገነ።
Next article144 የአሽከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋማት በቴክኖሎጅ የታገዘ ሥልጠና እንዲሠጡ ተደርጓል።