የክልሉ መንግሥት የተፈጠረውን ችግር መርምሮ የታክስ ምሕረት ማድረጉ ለቀጣይ ሥራቸው ተስፋ እንደሚሰጥ አስተያዬታቸውን የሰጡ ባለሀብቶች ገለጹ፡፡

131

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት በተለያዬ ጊዜ በክልሉ በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች የንግድ ተቋሞቻቸው ለተጎዱባቸው አካላት የታክስ ምሕረት አድርጓል፡፡ በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች የንግድ ተቋሟቻቸው የተጎዱባቸው የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የታክስ ምሕረት እንዲደረግላቸው ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ተመላክቷል፡፡

ሚያዚያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሄደው የአማራ ክልል መሥተዳድር ምክር ቤት ከስምንት ዞኖች ለተውጣቱ ከ140 በላይ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት 15 ሚሊዮን 936 ሺህ 462 ብር ገደማ የታክስ ምሕረትን አጽድቋል፡፡

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች አንዳንድ የንግድ ተቋማት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ብዙዓየሁ ቢያዝን በየደረጃው ባሉ የታክስ አጣሪ ኮሚቴዎች 66 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የምሕረት ጥያቄ ቢቀርብም ቢሮው ተገቢነት አላቸው ያላቸውን አጣርቶ የ140 የንግድ ተቋማትን ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የታክስ ምሕረት ለመሥተዳድር ምክር ቤቱ እንዲጸድቅለት ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

መሥተዳድር ምክር ቤቱም በአስቸኳይ ስብሰባው በየደረጃው የነበረውን የማጣራት ሂደት፣ ተገቢነት እና በቀጣይ የሚፈጥረውን አዝማሚያ መርምሮ እና ተወያይቶ የቀረበውን የታክስ ምሕረት አጽድቆታል፡፡

አብመድ በስልክ አስተያዬታቸውን የጠየቃቸው እና ምሕረት የተደረገላቸው የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትም የታክስ ምሕረቱ ለቀጣይ የንግድ እንቅስቃሴያቸው አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አሰማረው መኮንን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ከሚያለሙት መሬት ውስጥ 377 ሄክታር እስካሁን እንዳልታረሰ ገልፀዋል፡፡

“ማምረት ባልቻለ መሬት ላይ ግብር መክፈል ይከብዳል” ያሉት አቶ አሰማረው “የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት ችግሩን መርምሮ የሰጠው ውሳኔ ኢንቨስትመንታችን ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ያግዛል” ብለዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማ ነዋሪና በሆቴል አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ማስረሻ ሳኅሌ ደግሞ ባለፈው ዓመት በአካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ድርጅታቸው ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ በተፈጠረው ችግር አገልግሎት መስጠት ያቆሙት አቶ ማስረሻ ‘‘መንግሥት ያደረገው የታክስ ምሕረት አገልግሎቱን መልሶ ለማደራጀት ያግዛል’’ ብለዋል፡፡ መንግሥት የተረጋጋ የኢንቨስትመንት አካባቢ እንዲፈጥርላቸውም ጠይቀዋል፡፡

‘‘አሁን በመሥተዳድር ምክር ቤቱ የጸደቀው የታክስ ምሕረት በየደረጃው ባሉ አጣሪ ኮሚቴዎች ታይቶ የቀረበ ብቻ ነው’’ ያሉት የአማራ ክልል የገቢዎች ቢሮ ኃላፊዋ የክልሉ የታክስ አጣሪ ኮሚቴም በየቦታዎቹ በመሄድ ትክክለኛነቱን እንዳረጋገጠም ተናግረዋል፡፡ ከሰሞኑ የመሥተዳድር ምክር ቤቱ እንዲያጸድቀው የቀረበው በየደረጃው ባሉ አጣሪ ኮሚቴዎች ተጣርቶ ለቢሮው የደረሰው እና ቢሮው ያረጋገጠው ብቻ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎች የሚቀርቡ የምሕረት ጥያቄዎች ተመርምረው ሲቀርቡ ቢሮው አረጋግጦ ለምክር ቤቱ እንደሚያቀርብም አስታውቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleየአስቸኳይ ጊዜ አወጁን ለማስከበር የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚደረግ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
Next articleየተከዜ ዓሳ ሀብትን ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎች ለአራት ወረዳዎች ተሰጡ።