
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የክልሉን መንግሥት ያመሰገነው የዳኞች ጥበቃ እና ከለላ የተካተተበትን የአማራ ብሔራዊ ክልል ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ ምክር ቤቱ መርምሮ በማጽደቁና ዉሳኔው ነፃ የዳኝነት አካል ለመገንባት የክልሉ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት በማሳየቱ እንደኾነ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አለምአንተ አግደው አስታውቀዋል።
ጉዳዩን አስመልክቶም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለአሚኮ በላከው መግለጫ የአማራ ብሔራዊ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በመሠረታዊነት በማሻሻል የኅብረተሰቡን እርካታ ያረጋገጡ እና በሕዝብ ዘንድ አመኔታ የተቸራቸው ፍርድ ቤቶች ለመገንባት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ከ10 ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ የተቀዳ የ2017 ዓ.ም የበጀት ዓመት ዓመታዊ መሪ ዕቅድ፣ ከሀገራዊው የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር የተናበበ እና የክልሉን ፍርደ ቤቶች ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የተከለሰ የፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እና የ100 ቀናት ዕቅድ በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱን አመላክቷል፡፡
በተጓዳኝም የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረከን በማስተባበር እና የስምምነት ቻርተር በመፈራረም እንዲሁም የ2017 ዓ.ም የበጀት ዓመት ዓመታዊ ዕቅድ በማቀድ የተቋማቱ ነጻነት እንደተጠበቀ ሆኖ የወል በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በመግለጫው እንዳስታወቀው የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን እንዲደገፍ በማድረግ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ እና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ማስፈን ወቅቱ የሚጠይቀው ቁልፍ ተግባር ነው፤ ለዚህም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዲጂታላይዜሽን ፕሮጀከት ጽሕፈት ቤት ቀርጾ ከፍ ያለ እንቅስቀሴ እየተደረገ ሲሆን በዚህ ረገድ ቀድመው ወደ ስራ ከገቡ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርደ ቤት፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከኦሮሚያ ከልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ከብሔራዊ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ እና ሌሎች መሰል የቴክኖሎጂ ተቋማት ልምድ ቀስሟል፤ ተግባራዊ ለማድረግም ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ እና በመስኩ ልዩ እውቀት፣ የካበተ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን እና የተለያዩ ተቋማት የበላይ አመራሮችን ያካተተ የዐቢይ እና ቴክኒካል ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክቱን በመንግሥት በሚመደብ በጀት ብቻ ለመተግበር አዳጋች መሆኑን በመገንዘብ የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በማቋቋም ድጋፍ የማፈላለግ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝና ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ከደጋፊ እና አጋር አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራቱ አመርቂ ውጤት መመዝግቡን ነው የተገለጸው፡፡
የታቀዱ ዕቅዶችን ለመተግበር እና በሀገር አቀፍ ድረጃ ምሳሌ የሚሆን የዳኝነት አካል የመገንባት ራዕይ እውን ለማድረግ የለውጥ ኀይል ማደራጀት ግድ የሚል በመሆኑ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የአይሲቲ ዳይሬክቶሬትን ጨምሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት እና የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬከቶሬትን እንደገና በማደራጀት ብቃት፣ ልምድ እና ከህሎት ያላቸው ባለሙያዎች ተመድበው እንዲሠሩ መደረጉንም መግለጫው አብራርቷል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን መልካም ጅምር በማየት የከልሉ መንግሥትም ለዲጅታላይዜሽን ስራዎች 300 ሚሊዮን ብር በጀት በመፍቀድ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በኢትዮ ቴሌኮም መካከል ከ219 ሚሊዮን ብር በላይ ውል እና መግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ደረጃ የኔትወርክ ዝርጋት የመለስተኛ ዳታ ቋት፣ የደኅንነት ካሜራ ሥርዓት እና የኦዲዮ ቪዥዋል ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የዳኞችን የጉባኤ ተሿሚዎችን እና የአሥተዳደር ሠራተኞችን የመፈጸም አቅም ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፤ ይህም በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የ6 ወራት ሥራ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይጊዜ ጋር ሲነጻጸር ብልጫ ያለው እንዲሆን መደረጉን ነው ያስታወቀው፡፡ ለአብነት ያህልም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በእረፍት ጊዜያቸው ሳይቀር በመስራት ከቀረቡ 2 ሺህ መዛግብት ውስጥ 1 ሺህ 920 ለሚሆኑት መዛግብት እልባት መስጠታቸው የተሰጡ ስልጠናዎች የዳኞችን የሥራ ተነሳሽነት ከፍ ያደረጉ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ነው የተመላከተው፡፡
በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የ6 ወር የመዝገብ ከንውንን በሚመለከት ምድብ ችሎቶችን ጨምሮ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ባህር ዳር ምድብ ችሎት 4048 መዝገቦች ለሰበር ሰሚ ችሎት ቀርበው 2794 መዝገቦች እልባት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይሄም ከባለፈው ተመሳሳይ ግማሽ የበጀት አመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ27 ነጥብ 37 በመቶ ብልጫ ያለው እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል። ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ደሴ ምድብ ሰበር ሰሚ ችሎት 1 ሺህ 651 መዛግብት የቀረቡ ሲሆን 1 ሺህ 180 ያህሉ እልባት አግኝተዋል፡፡ ለመደበኛ ችሎት ደግሞ 1 ሺህ 350 መዛግብት ቀርበው 876 መዛግብት እልባት ያገኙ ሲሆን ከባለፈው ተመሳሳይ የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ4 ነጥብ 88 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት የመዝገብ አፈጻጸም ሲታይ ደግሞ በባሕር ዳር ምድብ ችሎት 1 ሺህ 284 የፍትሕ ብሔርመዛግብት ቀርበው 685 መዛግብት ውሳኔ አግኝተዋል፡፡ ይሄም ከባለፈው ተመሳሳይ ግምሽ የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ12 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ አለው። የወንጀል መዛግብትን በተመለከተም 600 መዛግብት ቀርበው፣ 515 ውሳኔ አግኝተዋል፡፡ አፈጻጸሙ ከባለፈው ተመሳሳይ ግማሽ የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 29 ነጥብ 54 በመቶ ብልጫ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጎንደር ምድብ ችሎት 519 መዛግብት ለስራ የቀረቡ ሲሆን፣ 217 መዛግብት አልባት አግኝተዋል፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ደብረብርሃን ምድብ ችሎት 354 መዛግብት ለስራ የቀረቡ ሲሆን፣ 287 ያህሉ እልባት ያገኙ ሲሆን ከባለፈው ተመሳሳይ የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ5 ነጥብ 69 በመቶ ብልጫ አለው።
በአጠቃላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የመዝገብ አፈጻጸም ከባለፈው ተመሳሳይ ግማሽ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ4 ነጥብ 88 እሰከ 29 ነጥብ 54 የሚደርስ ብልጫ አሳይቷል፡፡ የዳኝነት አገልግሎት ጊዜን ለመቀነስ በተሰራ ሰፊ የንቅናቄ ስራ መዝገብ አልተመረመረም በሚል ይሰጡ የነበሩ ተለዋጭ ቀጠሮዎችን መቀነስ ብሎም ማስቀረት የተቻለ ሲሆን ዳኞች በእረፍት ጊዚያቸው ሳይቀር መዝገብ መስራታቸው፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ያስቀርባል እያስቀርብም ውሳኔ በዕለቱ ተመርምሮ ውሳኔ መሰጠት መቻሉ፣ የዳኞች የእጅ ጽሑፍ ቀርቶ ውሳኔዎች እና ትዕዛዞች በኮምፒውተር እየተጻፉ መሆኑ፣ የስራ ማነቃቂያ ስልጠናዎች መሰጠታቸው እና የ2017 ዓ.ም የበጀት ዓመት የሥራ ማስጀመሪያ ንቅናቄ መደረጉ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የመዝገብ አፈጻጸም ከፍ እንዲል እንዳደረገው ተገልጿል፡፡
የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የመዝጉብ ክንውን ሲታይ 25 ነጥብ 594 የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ቀርበው 15 ሺህ 701 መዛግብት እልባት አግኝተዋል፡፡ ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ የበጀት ዓመት ጋር በንጽጽር ሲመዘን የ7 ነጥብ 93 ብልጫ እንዳለው የሚያሳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ 172 ሺህ 698 የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ለወረዳ ፍርድ ቤቶች ቀርበው 139 ሺህ 050 ያህሉ እልባት የተሰጣቸው ሲሆን ከባለፈው ተመሳሳይ የበጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 33 ብልጫ እንዳለው ተጠቅሷል፡፡
በጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ እልባት ካገኙት መዛግብት መካከል 4 ሺህ 098 ከ6 ወር በታች የዕድሜ ቆይታ ያላቸው ሲሆን፣ 1 ሺህ189 ከ6 ወር እስከ 1 ዓመት የዕድሜ ቆይታ ያላቸው ናቸው። 1 ሺህ 540 የሚሆኑት መዛግብት ደግሞ ከ1 ዓመት በላይ የዕድሜ ቆይታ ያላቸው ናቸው፡፡
በከፍተኛ ፍርድ ቤት ደረጃ እልባት ካገኙ 15 ነጥብ 701 መዛግብት ውስጥ 12, ሺህ 193 ከ6 ወር በታች የዕድሜ ቆይታ ያላቸው ሲሆኑ 1 ሺህ 952 ከ6 ወር እስከ 1 ዓመት የዕድሜ ቆይታ ያላቸው ናቸው:: 1 ሺህ 556 የሚሆኑት ከዓመት በላይ የእድሜ ቆይታ ያላቸው ናቸው።
በወረዳ ፍርድ ቤቶችም እልባት ካገኙት 139 ሺህ 050 መዛግብት ውስጥ 122 ሺህ 165 የሚሆኑት ከ2 ወር በታች የእድሜ ቆይታ ያላቸው ሲሆን 12 ሺህ 981 የሚሆኑት ደግሞ ከ 2 ወር እስከ 6 ወር የዕድሜ ቆይታ ያላቸው ሲሆኑ፣ 2 ሺህ 806 የሚሆኑት ከ6 ወር እሰከ 1 ዓመት የእድሜ ቆይታ ያላቸው ናቸው። 1 ሺህ 098 ያህሉ ደግሞ ከዓመት በላይ እድሜ ቆይታ ያላቸው ናቸው።
በሌላ በኩል በጠቅላይ ፍርድ ቤት ታይተው በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ከታዩት መዛግብት መካከል 88 ነጥብ 5 በመቶ የመጽናት ምጣኔ ለማድረስ እቅድ ተይዞ አፈጻጸሙ 76 ነጥብ 89 በመቶ ሲሆን በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ታይተው በጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ ወይም በሰበር ከታዩት መዛግብት መካከል 85 ነጥብ 5 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ አፈጻጸሙ 70 ነጥብ 25በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ በወረዳ ፍርድ ቤት ታይተው በከፍተኛ ፍርድ ቤት የመጽናት ምጣኔን 80 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ አፈጻጸሙ 60 ነጥብ 26 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም በፍርድ ጥራት ረገድ ችግር ያለ መሆኑን ስለሚጠቁም ከፍተትን የለዬ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ ስልጠናዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
በተከላካይ ጠበቆች ነጻ የህማ ድጋፍ የተሰጣቸው በወንጀል የተከሰሱ ሰዎችን በሚመለከት በ2 ሺህ 030 መዛግብት ላይ 2 ሺህ 777 ተከሳሾች ነጻ የሕግ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ የተለያዩ ቅጻቅጾችን በማዘጋጀት 104 ሺህ 121 ባለጉዳዮች በነጻ እንዲጠቀሙ በማድረግ ለቅጾቹ ሊያወጡት የነበረን ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማስቀረት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ወንድ 851 ፣ ሴት 638 ፣ ድምር 1 ሺህ 489 አካል ጉዳተኞች ፤ አረጋዊያንን በተመለከተ ደግሞ ወንድ 2712፣ ሴት 2605፣ በድምሩ 5 ሺህ 317 እንዲሁም ለህጻናት በተደረገ ልዩ ድጋፍ ወንድ 2 ሺህ144 ፣ ሴት 4 ሺህ 862 ፣ በድምሩ 7 ሺህ 006 ባለጉዳዮች በአጠቃላይ በልዩ ትኩረት አገልግሎት ለሚሹ 12 ሺህ 323 የሚሆኑ የማኅበረሰብ ከፍሎች አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተጀመሩ ሥር ነቀል የለውጥ ሥራዎችን በተገቢው ለመተግበር ይችል ዘንድ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ይህም የተቋሙ የለውጥ ስራዎች ተገቢው ስርአት እንዲበጅላቸው የሚያደርግ እና ዘላቂነቱን የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ የአማራ ብሔራዊ ክልል ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ፣ የሕግ እና የፍትህ ኢንስቲትዩትን እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀ አዋጅ ፣ በአማራ ብሔራዊ ክልል የባህል ፍርድ ቤቶች ለማቋቋምና እውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ አዋጅ ፣ የእማራ ብሔራዊ ክልል ተከላካይ ጠበቆች አዋጅ እና የአማራ ብሔራዊ ክልል የዳኝነት አገልግሎት ክፍያን ለመወሰን የተዘጋጀ ደንብ ዝግጅት ተጠናቆ ለክልሉ ምክር ቤት እንደተላኩ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለምክር ቤቱ ያቀረባቸው ሶስት አዋጆች እና አንድ ደንብ የጸደቁ ሲሆን፣ በተለይም የአማራ ብሔራዊ ከልል ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ በየደረጃው ያሉ ዳኞች፣ መላው የተቋሙ ሠራተኞች እንዲሁም የዳኝነት ነጻነት የሚገዳቸው በሙሉ አጥበቀው ሲሹት የኖሩት ጉዳይ በመሆኑ የአዋጁ መጽደቅ በክልላችን የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ሥራ ውስጥ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው ብሏል፡፡
ለዳኞች ጥበቃ እና ከለላ መስጠት የግለሰብ ዳኛ ጉዳይ ሳይሆን አጠቃላይ የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓቱ ጉዳይ በመሆኑ፣ ለጸደቁት አዋጆች እና ደንብ ተፈጻሚነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጠየቀ ሲሆን፣ የቀጣይ ሥራ ለአዋጆቹ እና ደንቡ ተፈጻሚነት መስራት በመሆኑ በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚ አካላት እና በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር የሚሠሩ፣ የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ የዳኝነት ነጻነት እና የሕግ የበላይነት የሚገዳቸው በሙሉ የአማራ ብሔራዊ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለጀመራቸው ሁሉ አቀፍ የለውጥ ሥራዎች መሳካት አብረውት እንዲሠሩ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
የዳኞች ጥበቃ እና ከለላ የተካተተበት የአማራ ብሔራዊ ክልል ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ እና ሌሎችንም ምክር ቤቱ መርምሮ በማጽደቁ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አለምአንተ አግደው፣ ለክልሉ መሥተዳደር በተለይም ለክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት፣ ለክብርት አፈ ጉባኤ፣ ለሕግ፣ ፍትህ እና አሥተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ወጥ የሆነ ግንዛቤ እንዲያዝበት ለማስቻል እና ያሉ ክፍተቶችን ለማረም በማሰብ 187 ከሚሆኑ የምሥራቅ አማራ ቀጠና ፍርድ ቤት እና የፍትሕ አካላት አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር በደሴ ከተማ፣ በምዕራብ አማራ ቀጠና ካሉት መካከልም 160 ከሚሆኑ በባሕር ዳር ከተማ፣ እንዲሁም የማዕከላዊ ጎንደር እና አዋሳኝ ዞኖች እና ወረዳዎችን ጨምሮ 210 ከሚሆኑ በጎንደር ከተማ እና 142 ከሚሆኑ የሰሜን ሸዋ የፍርድ ቤት እና የፍትሕ አካላት አመራች እና ባለሙያዎች ጋር በደብረ ብርሃን ከተማ ውይይት መደረጉንም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ በዚህም የትብብር መድረኩ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ተረጋግጧል ነው ያለው፡፡
የበጀት እጥረት፣ የቢሮ እና የማስቻያ ቦታዎች እጥረት፣ የዳኞች የመኖሪያ ቤት ችግር፣ የተሽከርካሪ እጥረት፣ አንዳንድ አካላት የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ለመፈጸም የእምቢተኝነት አዝማሚያ ማሳየታቸው እና መሰል ችግሮች ደግሞ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ነበሩ፤ ችግሩን ፍርድ ቤቱ ለክልሉ ምክር ቤትም በሪፖርቱ ያቀረበ ሲሆን ከክልሉ መንግሥት እና ተቋሙ በራሱ አቅም እንዲሁም ረጂ አካላት ጋር በመተባበር የሚቀረፍበትን መንገድ ትኩረት በመስጠጥ በቀጣይ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡