
ባሕር ዳር: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን በየደረጃው ከሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና አጋር አካላት ጋር በ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ መሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ ተደራሽነቱ እና ደኅንነቱ የተረጋገጠ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት መስጠት የባለሥልጣኑ የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት መስኮች እንደነበሩ በውይይቱ ተነስቷል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደጄኔ በቀለ በ2017 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከ2 ሚሊዮን 200 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የኅብረተሠብ ክፍሎች የመንገድ ትራፊክ አደጋን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል ብለዋል።
ኀላፊው በዞኑ በተሽከርካሪዎች ላይ የሕግ የቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት ተደርጎ ተሠርቷል ነው ያሉት። በዚህም ጥፋተኛ ኾነው በተገኙ 9 ሺህ 247 ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል ነው ያሉት።
አሽከርካሪዎችን ማሠልጠን፣ የውሥጥ እና የውጭ የትራንሥፖርት አገልግሎት የኢንሥፔክሽን ሥራ እና የተሽከርካሪዎችን ዓመታዊ ምርመራ ትኩረት የተሠጣቸው ጉዳዮች መኾናቸውን ገልጸዋል።
ትርፍ እና ታሪፍን የተመለከቱ ሕጎች በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ማስከበር እና የአገልግሎት አሠጣጥን ማዘመን በቀጣይ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸውም ብለዋል።
የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዘውዱ ማለደ ባለፉት ስድስት ወራት የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የመረጃ ማዕከል በማቋቋም የአሽከርካሪ እና የተሽከርካሪ መረጃዎችን በሲስተም እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል። የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ “144 የአሽከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋማት በቴክኖሎ የታገዘ ሥልጠና እንዲሠጡ ተደርጓል” ነው ያሉት።
በዚህም ብቁ ሠልጣኞችን ማፍራት ተችሏል ብለዋል። ለነባር አሽከርካሪዎች የትራፊክ ደኅንነት ትምህርት መሥጠት በመቻሉ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር አደጋን መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
በተያያዘ በትራንስፖርት ዘርፉ የተሠማሩ ባለሃብቶች ከ10 ሚሊዮን በር በላይ በማውጣት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ቤት ገንብተዋል። ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚኾን የትምህርት ቁሳቁስም ለተማሪዎች ድጋፍ አድርገዋል ተብሏል።
የአሚኮየአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን