ባሕር ዳርን በማልማት ነዋሪዎቿን ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለሃብቱ ጋር በትብብር እንደሚሠራ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

31

ባሕር ዳር: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ”ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት” በሚል መሪ መልዕክት ከከተማ አሥተዳደሩ ባለሃብቶች እና አጋር አካላት ጋር የንቅናቄ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ተሸጋገረ የሚባለው ኢንዱስትሪ የመሪነት ድርሻውን ሲረከብ መኾኑን ገልጸዋል። የውይይቱ ዓላማ አምራች ኢንዱስትሪው ውጤታማ እንዲኾን የመንግሥት እና የግል አምራቾችን በማስተሳሰር የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ከውጭ የሚመጣውን ሸቀጥ መተካት እና ምርት ወደ ውጭ በመላክ ዶላር ማምጣት መኾኑንም አመላክተዋል።

በባሕር ዳር ከተማ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ በተደረገ ጥረትም ላመለከቱ 700 ፕሮጀክቶች ተፈቅዶ 214 ወደ ምርት ገብተዋል፤ 200 ደግሞ በግንባታ ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል። ሥራ ባልጀመሩ 40 ፕሮጀክቶች ላይ ደግሞ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል። ችግሮች ይኖራሉ ነገር ግን ተደናቅፋችሁ ሳትወድቁ ችግር ተቋቁማችሁ አብራችሁን ለዘለቃችሁ፣ ምጣኔ ሃብቱ እንዳይቀዛቀዝ ኀላፊነት ወስዳችሁ የሠራችሁ ምሥጋና ይገባችኋል ብለዋል።

ወደፊትም በችግሮች ብንፈተን ችግሮችን እንደምንሻገር በማመን እጅ ለእጅ ተያይዘን ሕዝባችን እና ሀገራችን ማሻገር ይጠበቅብናል ብለዋል። ለአምራቹም ኾነ አገልግሎት ሰጭው ኢንዱስትሪ አሥተዳደራቸው ለመደገፍ ዝግጁ መኾኑን አቶ ጎሹ ቃል ገብተዋል። የአገልግሎት አሰጣጡን ችግር መፍታት መጀመሩን እና ከባለሃብቱ ጋር በመደጋገፍ ከተማዋን እንደሚያለሙ ተናግረዋል።

”በቢሮ እና በኮሪደር የጀመረው ልማት በየቤቱ ገብቶ የሰው ሕይዎት ሲቀየር ነው ልማቱ ልማት የሚኾነው” ብለዋል። ለዚህም የአመራሩ እና የባለሃብቱ ተመካክሮ መሥራት ወሳኝነት እንዳለው ጠቅሰዋል። ከተማ አሥተዳደሩም የጀመረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሳለጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ ባሕር ዳርን ማስዋብ ብቻ ሳይኾን ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግ ጭምር እንደኾነም አስገንዝበዋል።

በዚህም ነዋሪው ጣናን በግልጽ እንዲያገኘው እና ነፋሻ እና ቀዝቃዛ አየሩን እንዲጠቀምበት ይደረጋል ብለዋል።

ባሕር ዳር በሁሉም ዘርፍ አድጋ እና በልጽጋ ሞዴል ከተማ እንድትኾን የክልሉ መንግሥት ለሚያደርገው ጥረትም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አመሥግነዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ሕጋዊ ተጠያቂነት!

Previous article“38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በስኬት ተጠናቅቋል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next articleየምክክር ኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ተራዘመ።