
አዲስ አበባ: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 46ኛው የአሥፈጻሚዎች ጉባኤ መጠናቀቅን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ መግለጫ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ በቂ ዝግጅት በማድረግ አንድ ንጉስ፣ 30 ፕሬዝዳንቶች፣ አምስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና 17 ቀዳማዊት እመቤቶች እና ሌሎች ሀገራት ደግሞ በሚኒስትሮቻቸው በኩል ተወክለው መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
“ከ17 ሺህ በላይ እንግዶች በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ተሳትፈዋል” ያሉት አምባሳደር ብርቱካን 12 ሺህ እንግዶች ከውጭ ሀገር መጥተው የተሳተፉ ናቸው ብለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሚመራ 35 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተካተቱበት እና 229 የዲፕሎማሲ አሥተባባሪዎች ጉባኤውን አሳልጠው በስኬት ተጠናቅቋል ነው ያሉት።
ዓለም አቀፍ የእንግዳ አቀባበል ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ መስተንግዶው ተካሂዷል ነው ያሉት። 57 ልዩ ፕሬዝዳንታዊ ቻርተሮች በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተስተናግደዋልም ብለዋል። የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እና የስድስት ኮሚሽነሮች ምርጫ በመኖሩ ምክንያት ከበርካታ ሀገራት የመጡ ሚዲያዎች የጉባኤው ድምቀት ነበሩም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ባለፈ የንግድ ማዕከልም መኾን የሚያስችላትን መሠረት የጣለችበት ነው ብለዋል። ጉባኤው ኢትዮጵያ በርካታ ጉዞዎችን አድርጋ ልትሠራው የምትፈልገውን ዲፕሎማሲ ወጭ ቆጣቢ በኾነ መንገድ ከኅብረቱ ጉባኤ ጎን በርካታ ሥራዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) እና በምክትላቸው አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኩል ሰፊ ተግባር ተሠርቷል ነው ያሉት በመግለጫቸው።
ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምስጋና አቅርቧል።
ዘጋቢ: አንዷለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!