“አቅማችንን አሟጠን ከሠራን ለውጥ ቅርብ ነው” ከንቲባ አዳነች አቤቤ

52

አዲስ አበባ: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ከህሎት ቢሮ ለስድስት ወራት በአለማማጅ ድርጅቶች ወስጥ የተግባር ሥልጠና የወሰዱ ከ13 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለሁለተኛ ጊዜ አስመርቋል። የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ እና ክህሎት ቢሮ ለወጣቶች የሥራ ዕድልን ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሥራ የሌላቸው ወጣቶችን በመመልመል በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዙር ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ እንዲወስዱ ተደርጓል። ከ20 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ጥራቱ በየነ ተናግረዋል።

የብቃት ለወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ምንም ሥራ ሳይኖራቸው ቤት የተቀመጡ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 25 የኾኑ ወጣቶችን በመመልመል እየሠራ ይገኛል። ይህ መርሐ ግብር ከተጀመረበት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በመጀመሪያው ዙር የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ከ7 ሺህ በላይ ወጣቶችን ማስመረቅ እንደተቻለ ተናግረዋል።

በ2ኛ ዙር ደግሞ ከ13 ሺህ በላይ ወጣቶች በብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ሥልጠና እንዲወስዱ እና የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ስለመደረጉ አስገንዝበዋል። የከተማ አሥተዳደሩ እየሠራው ባለው የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ዘርፍ በሁለቱም ዙር ከ21 ሺህ 283 በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸውም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሀገር የሚገነባው በወጣቶች ነው ብለዋል። ወጣቶች ራሳቸውንም ኾነ ሀገራቸውን ለመለወጥ አዲስ እሳቤ በመያዝ የተፈጠረላቸውን ዕድል እንዲጠቀሙም አሳስበዋል። ከንቲባ አዳነች መንግሥት ሥራ በክህሎት መመራት አለበት በሚል እሳቤ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ሁሌም አቅምን አሟጦ መሥራት ከተቻለ ለውጥ ቅርብ በመኾኑ ወጣቶች ጠንክረው እንዲሠሩ አሳስበው ለዚህም የከተማ አሥተዳደሩ ሁሌም ከጎናቸው እንደሚኾን ነው ያስገነዘቡት። ሦስተኛው ዙር የብቃት ለወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ በ40 ወረዳዎች ከ15 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ መጀመሩንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሦተኛው ዙር ከ3ሺህ 600 በላይ ተማሪዎችን መመዝገብ መቻሉን የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
Next article“38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በስኬት ተጠናቅቋል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር