
ፍኖተ ሰላም: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመማር ማስተማር ሥራ በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተና የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። ትምህርት ባልተጀመሩባቸው አካባቢዎች ሶስተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ እስከ የካቲት 30/2017 ዓ.ም ድረስ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም መምሪያው ገልጿል።
በከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች ሊኖሩ አይገባም በሚል አስተሳሰብ በጸጥታ ችግር ምክንያት መማር ማስተማር የተቋረጠባቸውን ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ለማስጀመር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደረጀ ታደሰ ተናግረዋል።
አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የመማር ማስተማር ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ያነሱት ደግሞ የቡሬ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አንማው ብዙአየሁ ናቸው። በተለይም መማር ማስተማር በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች በ2017 በጀት ዓመት የሚሰጠውን ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተና ውጤትን ለማሻሻል በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ኀላፊዎቹ አንስተዋል። ለዚህም በተመረጡ መምህራን የማካካሻ ትምህርት እየተሰጠ እንደኾነ ተናግረዋል።
አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው እና ትምህርት ባልተጀመረባቸው አካባቢዎች በሶስተኛ ዙር እስከ የካቲት 30/2017 ዓ.ም ድረስ የተማሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ መኾኑን የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ መኩሪያው ገረመው ናቸው። በሶተኛው ዙር ከ3ሺህ 600 በላይ ተማሪዎችን መመዝገብ መቻሉንም ተናግረዋል። ተማሪዎች ክልላዊ እና ሀገራዊ ፈተናን ለማስፈተን በሚደረገው ጥረት ሁሉም አካል ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።
የአሚኮየአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን