የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር እንዲፈታላቸው የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

18

ደሴ: የካቲት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመካነ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ካለው የሕዝብ ብዛት አኳያ ለከተማው ሕዝብ የሚቀርበው ውኃ አነስተኛ በመኾኑ ችግሩን በከተማ አሥተዳደሩ አቅም መፍታት እንዳልተቻለም ተመላክቷል። የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች የቆየ ጥያቄ ኾኖ ቆይቷል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት እየተባባሰ በመጣው የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ከጉልበት እና ጊዜያቸው ባለፈ ለኢኮኖማያዊ ችግሮች እየዳረጋቸው ነው።

የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ሀብታሙ አማረ እና ሰብስቤ እንድሬ ውኃ ፍለጋ ከሌሊት ጀምሮ ወረፋ ለመጠበቅ እንደሚሄዱ ገልጸዋል። በቀን ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ሀብታሙ አማረ ከጉልበት እና ጊዜያቸው ብክነት በተጨማሪ ሥራቸውን እያጡ መኾኑን ተናግረዋል። አንድ ጀሪካን ውኃም እስከ 40 ብር እንደሚሸጥ ነው የጠቆሙት።

ሌላዋ አስተያየት ሰጭ ሀብታም አሰፋ ወረፋ ለመያዝ ሌሊት ሄደው ሳያገኙ የሚመለሱበት ጊዜ እንዳለ ገልጸዋል። በተለይ አቅመ ደካሞች እየተፈተኑ መኾኑን ነው የተናገሩት። የመካነ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ተስፋዬ ካሴ ከተማ አሥተዳደሩ ካለው የሕዝብ ብዛት አኳያ ለከተማው ሕዝብ የሚቀርበው ውኃ አነስተኛ መኾኑን ገልጸዋል።

“ችግሩን ለማቃለል በቅርቡ የተረከብነው የውኃ ጉድጓድ 27 ሊትር በሰከንድ ያመነጫል” ነው ያሉት። የውኃ ጉድጓዱ ታሽጎ በታሰበው ፍጥነት ወደ አገልግሎት ባለመግባቱ ችግሩ መባባሱንም ገልጸዋል። የሚመለከታቸው አካላት የሕዝቡን ችግር አይተው ትኩረት እንዲሰጡትም ጠይቀዋል። የመካነ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላኩ አያሌው የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግሩ የከተማዋን ልማት እንዲደበዝዝ አድርጎታል ብለዋል። ችግሩን ለመፍታት በየደረጃው ካሉ የመንግሥት አካላት ጋር እየሠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ፍሰሃ ዘውዱ የመካነ ሰላም የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው በተጀመረው የ”ሆጨጨ” ግድብ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመኾኑ እና እንደገና በፌዴራል ደረጃ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጉዳዩን ይዞ ከአማራ ልህቀት የዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ጋር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

አሁን ያለውን ችግር ለማቃለል በዋን ዋሽ በጀት ጥልቅ ጉድጓድ ተቆፍሮ 27ሊትር በሰከንድ የሚያመነጭ ጉድጓድ መገኘቱን አንስተዋል። ወደ አገልግሎት ለማስገባት ለአማራ ውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ተሰጥቷል ብለዋል ፓምፕ እና ሌሎች አስፈላጊ መሳሪያዎች ግዥን በተመለከተ በተለይም ለ”በጣሶ” የውኃ ጉድጓድ ችግር በዩኒሴፍ በጀት ጨረታ ወጥቶ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ግዥ እየተፈጸመ መኾኑን አስታውቀዋል።

ችግሩን እስከ ሰኔ 30 ድረስ ለመፍታት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ሙሐመድ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በጉባላፍቶ ወረዳ የሳንቃ ጤና ጣቢያን እየጎበኙ ነው።
Next articleየከተማዋን ኢንቨስትመንት የማነቃቃት ዓላማ ያለው ምክክር በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።