
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊዎች እና ቡድን መሪዎች ጋር የ2017 ዓ.ም የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው የባለፉት ስድስት ወራት ዘርፈ ብዙ የመኽር ሥራዎች የተሳለጡበት ዋነኛ ወቅት ነበር ብለዋል። ሁሉም ዓይነት የግብርና እንቅስቃሴዎች መከናዎናቸውንም አንስተዋል።
በበጋ መስኖ 342 ሺህ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ 254 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ እየለማ መኾኑን ተናግረዋል። ክልሉ 254 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል። እስካሁን 192 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈን ተችሏል ነው ያሉት። ቀሪው በሁለተኛ ዙር እና በበልግ እንደሚለማም ገልጸዋል። ክልሉ ለአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ምቹ በመኾኑም የተሻለ ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት።
የግብርና ሥራ ከአንዱ ወደ ሌላኛው ምዕራፍ የሚሸጋገር እንጅ የሚቋረጥ ባለመኾኑ አሁን ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማቱ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። አሁን ላይም በዘጠኝ ሺህ ተፋሰሶች ከ336ሄክታር በላይ መሬት የአፈር እና ውኃ ዕቀባ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
ለ2017/18 የምርት ዘመን 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል። 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መቅረቡንም ገልጸዋል። ለ2017/18 መኽር የአፈር ማዳበሪያ የአቅርቦት ችግር አይገጥመንም ያሉት አቶ አጀበ በማሰራጨቱ ሂደት ዕንቅፋት ይኾናሉ የተባሉ ሥጋቶችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል ብለዋል።
እንደ ክልል የአፈር ለምነትን የመጠበቅ እና የአፈር አሲዳማነትን ችግር ለማስወገድ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከሰብል ልማት ጎን ለጎን ለአረንጓዴ ዓሻራ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል ነው ያሉት።
በወቅቱ የተተከለው ችግኝ በአግባቡ ክብካቤ ስለተደረገለት ከ86 በመቶ በላይ ጸድቋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!