
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚዘወተር አንድ ተለምዷዊ አባባል አለ “ትምህርት የዕድገት መሠረት ነው” የሚል፡፡ እውነት ነው ትምህርት የዕድገት መሠረት ነው፡፡ ነገር ግን ትምህርት የዕውቀት ብርሃንን ካልገለጠ እና በተግባር ካልተገለጠ ብሂሉ የንግግር ማድመቂያ ከመኾን የዘለለ ረብ ያለው አይመስልም፡፡ ለአባባሉ እውነትነት ዛሬ ላይ ተምረው ያወቁ እና አስተምረው ያሳወቁ ሀገራት ያሉበትን ደረጃ መመልከት ብቻውን በቂ ማረጋገጫ ይኾናል፡፡
ትምህርት የዕውቀት መሠረት የኾነላቸው በርካታ የዓለም ሀገራት ማወቃቸው ለማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸው መፍትሔ የማፍለቅ ልዕልናን አጎናፅፏቸው ከውስንነቶቻቸው እና ከፈተናዎቻቸው በላይ ኾነዋል፡፡ የሳይንሱን፣ የቴክኖሎጂውን፣ የመንግሥት አሥተዳደሩን፣ የኪነ ጥበቡን፣ የሕክምናውን፣ የምሕንድስናውን… ልህቀት ደረጃ በደረጃ ደርሰውበታል፡፡ መቼም በዚህ “የመረጃ ዘመን” ላይ ቆመን ለዚህ ሐሳብ ማሳያ ጥቀሱ አንባልም፡፡ የአውሮፓውያኑን ምጥቀት እና የአሜሪካን ልዕለ ኀያልነት መመርመር ብቻውን በቂ ማሳያ ነው፡፡
ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በምትለው መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ የሀገራቸውን የትምህርት ሁኔታ ሲዳስሱ “በዓለም የሥልጣኔ መጀመሪያ ላይ አይደለንም፤ መጨረሻ ላይም አይደለንም፤ መካከል ላይ ነን” ይላሉ፡፡ ትምህርት ምንጊዜም በየትኛውም ሀገር ከዘመን እና ከቦታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከታሪካዊ ዕድሉ ለመድረስ እና ከዛሬው የሚበልጠውን የነገውን ታላቅነት በእጁ ለማድረግ ምርጫውም፤ አማራጩም አንድ ነው፤ ትምህርት ይላሉ፡፡
አድገዋል የምንላቸው ሀገራት ልምድ እና ተሞክሮ የሚያሳየው ትምህርት ምን ያህል በማኅበራዊ ጉዳዮቻቸው፣ በፖለቲካዊ ንቃተ ህሊናቸው፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መንገዳቸው አቅም እና ጉልበት እንደኾናቸው ነው፡፡ ብቁ እና በቂ የመፍጠር አቅም ያላቸው ዜጎችን ማፍራታቸው ሰፊውን ሕዝባዊ እና ሀገራዊ ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ እንዳስቻላቸው አርዓያ ኾኖ ይነሳል፡፡ የደኅንነት ስጋታቸውን ለመመለስ እና የኀይል ሚዛናቸውን ለማስጠበቅ ነፍጥ ያነገበ ሳይኾን ዕውቀት የጠገበ ዜጋ ነው ቀዳሚው ትኩረታቸው፡፡
ለዘርፉ በርካታ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈስሱበታል፤ እጥፍ ድርብ አድርገው ይካሱበታል፡፡ ትምህርትን በሚመለከት የእኛዋ ሀገርስ ምን ደረጃ ላይ ትገኛለች? ብሎ መጠየቅ እና መመርመር ችግሩን ለመሻገር ግማሽ መንገድ ያስጉዛል፡፡
ኢትዮጵያ የዜጎቿን የዕውቀት አድማስ ለማስፋት ዘመናዊውን የትምህርት ሥርዓት ዘርግታ እና ትምህርት ቤቶችን ገንብታ ማስተማር ከጀመረች ምዕተ ዓመት መሻገሯን ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ ቀደም ሲል ብራና ፍቀው ቀለም ለቅልቀው ፊደል ሲያስቆጥሩ የነበሩ ቤተ እምነቶቻችን አበርክቷቸው ላቅ ያለ ነው፡፡
ትምህርት በኢትዮጵያ ዘመኑን ዋጅቶ በዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ከፍ ወዳለ ደረጃ ይሸጋገር ተብሎም ብዙ ተለፍቶበታል፡፡ ውጤቱም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብዙም የከፋነው የሚያስብል እንዳልኾነ የዘርፉ ምሁራን ይስማማሉ፡፡
ከትናንት እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የነበረው አዝጋሚ ጉዞ በተደራሽነት እና ፍትሐዊነት ላይ የታዩ ለውጦች መኖራቸው አይካድም፡፡ ነገር ግን የዘርፉ ብርቱ ትችት ጥራት እና ተገቢነት ላይ የሚስተዋል ክፍተት እንደኾነ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ “የትምህርት ሥርዓታችን ሰው መሥራት አልቻለም” የሚለው ብርቱ ወቀሳ መልስ የሚሻ መሠረታዊ ክፍተት ኾኖ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ መምጣቱ አሳሳቢ እንዲኾን አድርጎታል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ክፉኛ ከተፈተኑ ተቋማት መካከል የትምህርት ዘርፉ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡ ግጭት፣ ጦርነት እና መፈናቀል የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማወኩ በላይ በርካታ የትምህርት ተቋማት ውድመት፣ ዝርፊያ እና ጥፋት አጋጥሟቸዋል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ጦርነቶች የትምህርት ተቋማት የጥቃት ሰለባ መኾናቸው ጉዳቱን በቀላሉ እንዳያገግም አድርጎት ቆይቷል፡፡
ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል በክልሉ የዘለቀው ግጭት ደግሞ ወትሮውንም በፈተና ውስጥ የነበረውን ዘርፍ ወደ ከፋ ምስቅልቅል ውስጥ ጨምሮታል፡፡ የትምህርት ተቋማት የጥቃት ዒላማ ከመኾናቸው ባሻገር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የነበሩ አስከፊ ጥቃቶች እና ዘመቻዎች የክልሉን ትምህርት ክፉኛ አጎሳቁለውታል፡፡
በተያዘው የትምህርት ዘመን ብቻ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸው የችግሩን አሳሳቢነት አጉልቶ ያሳያል፡፡ በትምህርት ጉዳይ ላይ መምከር ደግሞ የሁሉም ዜጋ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡
ለብዙ ጊዜ ሰው መሥራት አልቻለም እየተባለ የሚተቸው የትምህርት ሥርዓታችን ዛሬም ደግሞ በሰው ተፈትኗል፡፡ 4 ሚሊዮን ሕጻናት እና ወጣቶች ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም ማለት ትርጉሙ ከቁጥርም በላይ ነው፡፡ የችግሩ ጉዳት አሁን ሳይኾን ምናልባትም ከ10 ዓመታት በኋላ የሚታይ መኾኑ ዛሬ በጋራ ከመምከር እና ከመነጋገር የሚከለክል አይደለም፡፡ ስለትምህርት መነጋገር ስለትውልድ መምከር ነው፡፡
በታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን