
ወልድያ: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከፍላቂት ገረገራ ከተማ አሥተዳደር እና ከመቄት ወረዳ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ዙሪያ ምክክር አድርገዋል። በምክክሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ሰላምን የማረጋገጥ ተግባር ቀዳሚ አድርገን የምንሠራበት ጉዳይ ነው ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊቱ እና ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የሕዝቡን ፍላጎት የመጠበቅ ሥራ እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። የጸጥታ አካሉን ማገዝ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ጦርነት እያስከተለው ያለውን ጉዳት እያየነው እንገኛለን ያሉት አፈ ጉባኤዋ ሽማግሌዎች እስካሁን የሠራችሁት የሚበረታታ ነው፣ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ነው ያሉት።
ልንግባባበት የሚገባው ጉዳይ የትምህርት ጉዳይ ነው ያሉት አፈጉባዔዋ ልጆቻችን ላይ የምንፈልገውን ውጤት ማምጣት የምንችለው በትምህርት ነውና ኅብረተሰቡ ወደ ትምህርት ቤት መቅረብ እና መቀስቀስ አለበት ብለዋል።
በጸጥታ ችግር የገጠመንን የትምህርት ስብራት መንግሥት ብቻውን ሊጠግነው አይችልም ነው ያሉት። መንግሥት የመሪነት ሚናውን ለመወጣት ቁርጠኛ እንደኾነም ገልጸዋል። ኀብረተሰቡ ደግሞ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!