የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክና ከታማሚ ጋር ንክኪ የሌላቸው 19 ሰዎችን ጨምሮ በ25 ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ተገኘ፡፡

216

የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ያለፉት 24 ሰዓታትን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ውጤት ይፋ አድርጓል፤ በውጤቱ መሠረትም ለ1 ሺህ 847 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ በ25 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል፡፡ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ውስጥ 19ኙ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያልነበራቸውና የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ናቸው፡፡ ሦስቱ ደግሞ የውጭ ሀገር ጉዞ ያላቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ሦስት ከዚህ በፊት ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ተመላክቷል፡፡

ዛሬ ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጡት ውስጥ 21 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው፤ ሁለቱ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እና ሁለቱ ኦሮሚያ ክልል ናቸው፡፡ በቫይረሱ የተያዙት 24 ወንዶች ሲሆኑ አንዷ ሴት ነች፡፡ በዕድሜ ደረጃም ከ17 እስከ 65 ዓመት እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለ28 ሺህ 360 ሰዎች የናሙና ምርመራ ተደርጎ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥርም 187 ደርሷል፡፡ ባለፉት 24 ሰዓታት ያገገመ ታማሚ አለመኖሩ የተገለጸ ሲሆን አንድ ታማሚ በጽኑ ሕሙማን ክትትል ውስጥ እንዳለ ተመላክቷል፡፡

Previous article‘‘ለሕገ ወጥ የሰዎች ደላላ ምንም ዓይነት ምሕረት አያስፈልግም፤ ይህ አገርን እንደማጥቃት ይቆጠራል።” ዶክተር ስዩም መስፍን
Next articleየአስቸኳይ ጊዜ አወጁን ለማስከበር የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚደረግ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡