
ወልድያ: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከፍላቂት ገረገራ ከተማ አሥተዳደር እና ከመቄት ወረዳ ከተውጣጡ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል። የመድረኩ ተሳታፊ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ችግሮችን ለመፍታት ከግራም ከቀኝም ያሉት የሁላችንም ልጆች በመኾናቸው መክረን የሰላማችንን ጉዳይ በጋራ ማጽናት አለብን ብለዋል ተሳታፊዎቹ። በከተማዋ የተሠሩት የልማት ሥራዎችን ማየታቸውን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ነገም ከተማዋን እና ወረዳውን ከማልማት ወደኋላ እንደማይሉም አስረድተዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር ነዋሪዎቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች ቀደም ብለው የተያዙ ቢኾንም በአካባቢው ሰላም በመደፍረሱ አፋጣኝ መልስ ለመስጠት እንቅፋት ኾኖ ቆይቷል ብለዋል። ግብር ካልተሠበሠበ፣ ኢንቨስትመት ካልተስፋፋ፣ ንግድ ካልተሳለጠ የካሽ እጥረት ሊፈታ አይችልም ነው ያሉት።
የሸቀጥ እና የግብርና ምርት ከቦታ ቦታ በነጻነት መንቀሳቀስ አለመቻሉ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ምክንያት ኾኗል ብለዋል። እርስ በእርስ መገዳደልን እንደ ሕዝብ በመታገል ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ ለመውሰድ ሕዝብ ሊተባበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ ጥያቄዎችን በተደራጀ መንገድ ለመቀበል መገኘታቸውን አስረድተዋል።
ለተነሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች የሚመለከታቸው የቢሮ ኀላፊዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሠሩም ነው ያብራሩት። ለሁሉም ሥራ ቁልፉ ሰላም ነው፤ ሰላም ካለ ጥያቄዎች ይፈታሉ፤ ተንቀሳቅሶ ሀብት ማፍራት ይቻላል እና ለሰላም ሁሉም ዋጋ መክፈል እንደሚገባው አሳስበዋል።
ሰላም ከግል፣ ከቤተሰብ፣ ከማኅበረሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ የሚመነጭ በመኾኑ ሰላምን የማጽናት ጉዳይ ለተወሰኑ ቡድኖች ከመስጠት ይልቅ ሁሉም የድርሻውን ይወጣ ነው ያሉት። “መንግሥት የሚቀየረው በምርጫ ብቻ ነው፤ በኀይል ለማድረግ መሞከር አዋጭ አይደለም፤ በድምጻችሁ ሥልጣን ላይ ያስቀመጣችሁትን መንግሥት በምክንያት ላይ ተመስርታችሁ በሚቀጥለው ምርጫ ማውረድ ትችላላችሁ፤ ከዚህ ያፈነገጠ እና የተዛባ አመለካከት ይዘው ጫካ የገቡ ወገኖችን ግን ምከሩ” ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!