
ደብረ ብርሃን: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር እቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ በልቼ ቀበሌ አሥተዳደር በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ተመርቀዋል። አሚኮ ያነጋገራቸው በምርቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የቀበሌው ነዋሪዎች የመንገድ፣ የውኃ እና የመብራት ችግሮች እንደነበሩባቸው አንስተዋል።
እነዚህ ጥያቄዎች የቀበሌው መሪ እና ሕዝቡ እጅ እና ጓንት ኾኖ በመሥራቱ የልማት ጥያቄዎች በራስ የውስጥ አቅም ምላሽ ማግኘት ችለዋል ብለዋል። የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የተመረቁ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በኅብረተሰቡ ተሳትፎ የተሠሩ ስለመኾናቸው አብራርተዋል።
120 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጭ የተደረገባቸው እነዚህ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንደሚቻል ያሳዩ ናቸው ነው ያሉት። አቶ በድሉ የልቼ ቀበሌ አሥተዳደር ኅብረተሰብ እና መሪዎች በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾነው ጭምር መሥራት እንደሚቻል በተግባር ያሳዩ የከተማችን ምሳሌ ናቸው ብለዋል።
የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎቹን በክብር እንግድነት ተገኝተው የመረቁት የክልሉ ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) የክልሉ መንግሥት በአንድ እጅ የሰላም ማስከበርን፤ በሌላ እጅ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል ይገባል ብሎ የያዘውን አቋም በተግባር ያሳዬ ቀበሌ ነው ብለዋል።
በቀበሌው በኅብረተሰቡ ተሳትፎ የተሠሩ ሥራዎች የሚደነቁ ናቸው ያሉት ዶክተር ማማሩ ተሞክሮ የሚወሰድበት ሥራ እንደኾነም ተናግረዋል። የተሠሩ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ኅብረተሰቡ በተገቢው ሊጠብቃቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
በቀበሌው በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተሠሩት ሥራዎች የሦስት ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድን ጨምሮ፣ የጠጠር መንገድ፣ የውኃ፣ የመብራት ዝርጋታዎች፣ የቢሮ ማስዋብ እና የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታን ያጠቃለለ ነው።
ዘጋቢ፦ ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!