የትምህርት በሮች አለመከፈት የኋላ ኋላ ሀገርን ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም!

56

ባሕር ዳር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት እና የወደ ፊት የመቆሚያ ምሰሶ መኾኑ ይነገራል። ይህ ምሰሶ ሲዛነፍ አልያም ሲወድቅ ሀገርም ትጎዳለች። ይህን ያላሰቡ እጆች ይህን ምሰሶ ሲነቀንቁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታይተዋል፡፡ ሳያውቁም ይሁን አስበውበት ይህን ምሰሶ የሚነቀንቁ ከፊት የሚታየውን ትምህርት ለጊዜው የገደቡ ቢመስላቸውም ግን እውነታው ሀገርን ለመጉዳት የሚደረግ አንድ ሂደት ነው።

ዛሬ ላይ በአማራ ክልል ልጆች ከትምህርት ገበታ ርቀው እና የትምህርት ቤት ደጆች ናፍቀዋቸው ላየ እነዚህን ልጆች ወደ ትምህርት መመለስ አስፈላጊ መኾኑን ይረዳል፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ በከተማ ያሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለናፈቁ ልጆቻቸው ትምህርት መስጠት ጀምረዋል፡፡

ልጆቹም ከሚወዷቸው መምህሮቻቸው እና የትምህርት ቀለም ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ወሳኙ ጉዳይ ወደ ገጠር ያሉ ትምህርት ቤቶችስ የሚለው ነው፡፡ አሁን ላይ እንደሚታየው ብዙ የገጠር ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ናፍቀዋል፡፡ ተማሪዎቹም እንዲሁ ትምህርት መቼ ተከፍቶ ተምረን እያሉ ይገኛሉ፡፡

አቶ አስማረ አይቸው የተባሉ የተማሪ ወላጅ እንደነገሩን ትምህርት ተከፍቶ ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ጽኑ ፍላጎት አላቸው፡፡ልጆችን ለማስተማር የሚያስችል ሁኔታ መፈጠር አለበት ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ ወጣ ገባ ያልኾነ ሰላም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ልጆች እንዳይማሩ መከልከል ሀገርን ወደ ኋላ ማስቀረት ነው የሚሉት አቶ አስማረ ሁሉም በየድርሻው ቆም ብሎ ማሰብ አለበት ነው ያሉት። እኔ በትምህርት አልገፋውም የሚሉት አቶ አስማረ ልጄ ግን እንደኔ እንዲኾን ስለማልፈልግ ትምህርት እንዲቋረጥ ፈጽሞ አልፈቅድም ብለዋል፡፡

ትምህርት በመቋረጡ ሀገር እየሞተ እንደኾነ እረዳለው ነው ያሉት። የትምህርት ባለለድርሻ እና ወላጆች ተቀናጅተው በመሥራት ትምህርት እንዳይቀጥል የሚያደርጉ አካላትን ማስቆም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል ተብሎ መስማት እንደሀገር ወደፊት የሚያመጣው ውድቀት ከፍ ያለ ነው የሚሉት አቶ አስማረ ሁሉም በየፊናው ጉዳዩን አጢኖ ለመፍትሄ መምከር እና መዘጋጀት አለበት ነው ያሉት፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት በሰሞኑ ጉባኤው ላይ እንዳመላከተው የትምህርት ተሳተፎ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ የክልሉ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ቴክኖሎጂያዊ እድገት ቁልፍ መሳሪያው ትምህርት ነው ያለው ምክር ቤቱ ይህንንም ወሳኝ መስመር ጤነኛ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያመላከተው፡፡

ትምህርት ላይ ያለው ችግር ከፍ ያለ እንደኾነ ምክርቤቱ ገልጿል። ለዚህም እንደ ማሳያ በ2017 የትምህርት ዘመን 3 ሺህ 736 ትምህርት ቤቶች በክልሉ አለመከፈታቸውን ነው ያስገነዘበው፡፡ ይህም ክልሉ ከሌሎች ክልሎች ጋር ያለውን ተወዳዳሪነት ጥያቄ ውስጥ ጥሏል ነው ያለው።

ከ30 ሺህ በላይ መምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎች ደግሞ ወደ ትምህርት ቤታቸው ተገኝተው የመማር ማስተማር ሥራ ማከናወን አልቻሉም፡፡ ይህም የክልሉን የትምህርት ተሳትፎ አፈጻጸም 40 መቶ እንዲኾን አድርጎታል፡፡

ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሰላምን ችግር ሰንኮፉ ለይቶ ለመንቀል የሁላችን ሥራ ይጠይቃል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleመሪዎች እና ሕዝቡ በቅንጅት በመሥራታቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት እንደቻሉ የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።