
ወልድያ: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ከፍላቂት ገረገራ ከተማ አሥተዳደር እና ከመቄት ወረዳ ከተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ዙሪያ ምክክር አድርገዋል። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ከተሳታፊዎች ለተነሱ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች መላሽ ሰጥተዋል።
በምላሻቸውም ከወልድያ ጋሸና ያለው መንገድ ሰላም ከሰፈነ በፍጥነት ይሠራል ብለዋል። የንፁሕ መጠጥ ውኃ ጥያቄም ጊዜውን ጠብቆ መልስ ያገኛል ነው ያሉት። የከተማ ደረጃን ለማሻሻል ገቢን ማሳደግ የቅድሚያ ሥራ አድርጎ በመሥራት እና የከተማውን የኢኮኖሚ አቅም መለየት ይጠበቃል ብለዋል።
“የሰላምን ችግር ሰንኮፉ ለይቶ ለመንቀል የሁላችን ሥራ ይጠይቃል” ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ሰንኮፉን ለማወቅ ደግሞ ሁላችንም ስለ ሰላም እውነቱን በመናገር ከልብ መፈተሽ አለብን ነው ያሉት። አሁን ያለንበት ሁኔታ የአማራ ክልል ሕዝብ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለውን እውቅና የሚያሳንስ እና አሁንም በሀገር ግምባታ የራሱን ሚና እንዳይወጣ እንቅፋት የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ሰላም የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ግንባታ ውጤት እንደኾነም ገልጸዋል። እጃችንን ከእርሻ፣ ከንግድ እና ከመግንሥት አገልግሎት መሳሪያዎቻችን ጋር ሁሌም ሊጣመሩ ይገባል ነው ያሉት። የሃይማኖት ተቋማት ዘወትር ሰላምን መስበክ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ እየሠራ ያለው የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት ለመጠበቅ ነውና በሚከፍለው መስዋዕትነት ልክ ክብር እና ዝናውን ሕዝቡ ከፍ ሊያደርግለት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አቅርቧል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ከሽምግልና እስከ ድርድር በሩን ክፍት አድርጓል፤ በዚህም በሰላም ከመንግሥት ጋር የተቀላቀሉ በርካታ ናቸው ነው ያሉት። ይሁን እንጂ ዝርፊያ እና ውንብድናን ዓላማቸው ያደረጉ ዛሬም ጥሪውን አልተቀበሉም ብለዋል። አሁንም የሰላም በሩ ክፍት በመኾኑ ሕዝቡ ልጆቹን ወደ ሰላም የመመለስ ሥራውን ማጠናከር አለበት ነው ያሉት።
የዞንን እና የወረዳ መሪዎች ከሕዝባችሁ ጋር የወሰዳችሁት ተደጋጋሚ ሰላምን የመሻት ውይይት በደንብ ፈትሻችሁ ከሕዝባችሁ ጋር መግባባት ላይ ልትደርሱ ይገባል ነው ያሏቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!