
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ6ኛ እና 8ኛ ክፍሎች ክልላዊ ፈተና እና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፋዊ ፈተና የተማሪዎች ምዝገባ በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
በክልሉ የቀጠለው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ የጎላ ነው፡፡ የትምህርት ተቋማት ጉዳት፣ የተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መራቅ እና በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖው የከፋ ነው፡፡
በትምህርት ዘመኑ በክልሉ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ይሰጣሉ ያሉት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን የተማሪዎችን የፈተና ምዝገባ በኦንላይን ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ምዝገባም እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡
በቅርቡ ከክልል እስከ ወረዳ ካሉ የትምህርት ዘርፉ መሪዎች ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በሚመለከት ውይይት መደረጉን ያነሱት ኀላፊው ክልሉ ከገጠመው የተማሪዎች ምዝገባ ጎን ለጎን በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን በልዩ ሁኔታ ማብቃትም እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች ደረጃ ከኢንተርኔት መቆራረጥ ጋር በተያያዘ የተነሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን አንስተዋል። ችግሩን ለመፍታት ቢሯቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ከተፈጠረው ችግር አንጻርም ተማሪዎችን ከመመዝገብ ባለፈም ውጤታማ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ እገዛ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን