“በልዩ ሁኔታ ሦስተኛው ዙር የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

38

ባሕር ዳር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ለአንድ ዓመት ተኩል የዘለቀው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ የፈጠረው ጉዳት የከፋ ነው፡፡ ባለፈው የትምህርት ዘመን በትምህርት ገበታ ላይ ያሳለፉ ተማሪዎች ቁጥር 58 በመቶ ብቻ እንደ ነበር መረጃዎች ያመላታሉ፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን ለአሚኮ እንዳሉት በ2017 የትምህርት ዘመንም በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ቁጥር ከ50 በመቶ በታች ነው፡፡ የትምህርት ዘመኑን በግብዓት እና አቅርቦት በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርገን ብንጀምርም በተማሪዎች ምዝገባ እና መማር ማስተማር ሥራው ላይ የገጠመን ስብራት ምናልባትም ክልሉ በታሪኩ ገጥሞት የማያውቅ ይኾናል ብለዋል፡፡

በክልሉ በ2017 የትምህርት ዘመን 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ቢታቀድም እስካሁን ድረስ 4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ተማሪዎች አልተመዘገቡም ተብሏል፡፡ ተመዝግበው ትምህርት እየወሰዱ ያሉ ተማሪዎች ቁጥርም 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡

ቀደም ብሎ በተካሄደው “የትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄ ትምህርት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነጻ ኾኖ የተማሪዎችን የመማር መብት ማስጠበቅ እንደሚገባ በየደረጃው መግባባት ላይ ቢደረስም ውጤቱ ግን የሚጠበቀውን ያክል አልኾነም ነው የተባለው፡፡

ከነሐሴ 20/2016 ዓ.ም እስከ መስከረም 7/2017 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባ ተካሄዶ ትምህርት ተጀምሮ እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ በመኾኑ ሁለተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ ንቅናቄ ውስጥ እንድንገባ ተገድደናል ነው ያሉት፡፡

ከኅዳር 16/2017 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 21/2017 ዓ.ም በተካሄደው ሁለተኛ ዙር የተማሪዎች ምዝገባ ንቅናቄም ከ200 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

እንደ ክልሉ ሕዝብ ነባር የትምህርት እሴት እና ልምምድ ቢኾን የካቲት የተማሪዎች መመዝገቢያ ወቅት አልነበረም፡፡ ነገር ግን ክልሉን የገጠመው ስብራት እሱን እንዲያደርግ አስገድዶታል ነው ያሉት።

“በልዩ ሁኔታ ሦስተኛው ዙር የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው ከየካቲት 3/2017 ዓ.ም እስከ የካቲት 30/2017 ዓ.ም እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

የተማሪዎች ምዝገባ እስከ ሦስት ዙር የቀጠለበት ምክንያት በክልሉ መማር የሚገባቸው ሕጻናት እና ወጣቶች ወደ ትምህርት ገበታ ባለመምጣታቸው ነው ብለዋል፡፡ ትምህርት የተወዳዳሪነት ጉዳይ ነው ያሉት ኀላፊው ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት የችግሩን አሳሳቢነት በውል ተረድቶ እገዛ እና ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ከ19 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል” የማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ
Next article“ዛሬ ከእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጄላ ሬይነር ጋር በዋና ዋና የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት አድርጌያለሁ።