“ከ19 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል” የማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ

29

ባሕር ዳር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከታቀደው 4 ነጥብ 89 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 81 በመቶ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።

በቀጣይ ሦስት ዓመታት በአማራ ክልል ለ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅጣጫ ተቀምጧል። የሥራ ዕድል ለመፍጠር ቅድሚያ ከተሰጣቸው ውስጥ ደግሞ የማዕድን ዘርፍ አንዱ ነው። የማዕድን ሃብትም ከፍተኛ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም አለው። በ2017 በጀት ዓመት ለ45 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ በስድስት ወሩ ለ19 ሺህ 243 ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። በቀጣይ ስድስት ወራትም ወጣቶችን በዘርፉ ለማሰማራት እየተሠራ ይገኛል።

በማዕድን ልማት ለመሠማራት ቅድመ ዝግጅት ካጠናቀቁት ውስጥ ደግሞ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪ ሀብቶም፣ መብራቱ እና ጓደኞቹ ማኅበር አንዱ ነው። የማኅበሩ ሠብሣቢ ሀብቶም ዘለለው እንዳሉት አካባቢው በተለያዩ ማዕድናት የበለጸገ በመኾኑ በወርቅ ደለል ማምረት ሥራ ለመሠማራት የመቆፈሪያ ማሽን ከመከራየት ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች አድርገዋል።

በተያዘው ወርም ወደ ሥራ እንደሚገቡ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት በባሕላዊ መንገድ ይደረግ የነበረው ልማት አድካሚ አድርጎት መቆየቱን ያነሱት ሠብሣቢው ችግሩን ለመፍታት በማሽን ለመሥራት ማቀዳቸውን ነው የገለጹት። ምርቱን ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብም ውል ወስደዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የማዕድን መምሪያ ባለሙያ መለሰ በላይ እንዳሉት ዞኑ እንደ ወርቅ እና ኦፓል የመሳሰሉ ማዕድናት ይገኝበታል።

ባለሙያው እንዳሉት በዘርፉ 40 ማኅበራት በወርቅ ማምረት፣ 13 ማኅበራት ደግሞ በአሻዋ ማምረት ተደራጅተዋል። በእነዚህ ማኅበራት ለ2 ሺህ 483 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ከዚህ ውስጥ 582 ሴቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ታምራት ደምሴ እንዳሉት በ2017 በጀት ዓመት ለ45 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ በስድስት ወሩ ለ19 ሺህ 243 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። ከዚህ ውስጥ 76 በመቶ የሚኾኑት ወጣቶች ናቸው።

በቀጣይ ወጣቶችን በዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ማዕድናትን የመለየት ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል። በቅርቡ ወደ ሥራ በገቡ ፋብሪካዎች ወጣቶች እንዲሳተፉም ይደረጋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም አያሌ ዓመታትን የተሻገር ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article“በልዩ ሁኔታ ሦስተኛው ዙር የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ