
ጎንደር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፖርቲ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች እና ወጣቶች ክንፍ የስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማን በጎንደር ከተማ እያካሄደ ነው።
በግምገማው የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባል እና የሴቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዝዳንት መስከረም አበበ፤ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር)፣ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ፤ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ኀላፊ ኢለኒ ዓባይ፤ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የወጣቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋሁን ተሰማ እና በአማራ ክልል ያሉ የዞኖች እና ከተሞች የሴቶችና ወጣቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በግምገማው መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ጎንደር ታሪካዊ ተግባር የሠሩ የእቴጌ ምንትዋብ እና የሌሎች ጀግኖች ሴቶች መገኛ ናት ብለዋል። ሴቶች ሀገርን በመገንባት፣ ባሕልን በመጠበቅ፣ በዓድዋ ጦርነት የሃሳብ እና የተግባር ምንጭ በመኾን አገልግለዋል ነው ያሉት። ሀገራችን አሁን የገጠማትን የጸጥታ ችግር ለመቅረፍ ሴቶች የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ነው ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የምክር ቤት አባል፣ ምክትል ፕሬዝዳንት መስከረም አበበ፣ የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መስከረም አበበ የብሔራዊ ገዥ ትርክት ግንባታን ለማጠናከር፣ ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት፣ ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር ሴቶች እና ወጣቶች በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ነፍጥ አንግበው ወደ ጫካ የወጡ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመጡ እና ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ሴቶች እና ወጣቶች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል። የአማራ ክልል ብልጽግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) የሴቶች እና የወጣቶች ክንፍ ኅብረተሰብን የማንቃት፣ የማደራጀት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ተልዕኮ ያለባቸው አደረጃጀቶች መኾናቸውን ገልጸዋል። የሴቶች እና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
የሴቶች እና ወጣቶች ክንፍ አደረጃጀቶች ክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር በውይይት እንዲፈታ እና የሰላም አማራጭች እንዲተገበሩ፣ የታጠቁ አካላት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመጡ በትኩረት ሠርተዋል ብለዋል። በክልሉ በሌማት ትሩፋት፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በማኅበራዊ እና በፓለቲካ ዘርፍ የሴቶች እና የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት መሠራቱ በውይይቱ ተነስቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ሴቶችን በፓለቲካ፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መሥራታቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!