
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም(አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ፣ የሃሳብ መሪዎች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ፣ ይህንን ልዩነት እና አለመግባባት ለመፍታት ሰፋፊ ሀገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል፡፡
ኮሚሽኑ ይህንን ግብ ለማሳካት በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ሕዝባዊ ውይይቶችን በማካሄድ አጀንዳዎችን እያሳባሰበ ነው፡፡
በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ አጀንዳን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት መሰብሰብ ተቀዳሚ ግቡ መኾኑን ያነሳው ኮሚሽኑ ሂደቱ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን አይነት ቀጥተኛ ያልኾኑ በጎ አስተዋፅኦችን ለሀገር በማበርከት ላይ ነው፡፡
1. በዜጎች መካከል የተሻለ መተማመን እና ግንኙነትን ማዳበር
እየተከናወነ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ መሳተፍ የሚገባቸው ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡ ውይይቶቹ በተለያየ ፈርጆች በተለዩ ወገኖቻችን መካከል መተማመንን በመገንባት ተስፋ ሰጪ የኾኑ በጋራ የመሥራት ልምምዶች እንዲዳብሩ አስችለዋል፡፡
2. የባለቤትነት ስሜትን መፍጠር
የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈው በምክክር ሂደቶቹ መሳተፋቸው እና ለሀገር የሚጠቅሙ ሀሳቦችን ማንሳታቸው በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የኔነት ስሜት እንዲያዳብሩ እያስቻላቸው ይገኛል፡፡
3. የዲሞክራሲ ባሕልን ማሳደግ
ሀገራዊ ምክክር ከተደረገባቸው አብዛኛዎቹ ሀገራት ማስተዋል የሚቻለው ሂደቱን አካታችና አሳታፊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ይህም መሠረታዊ ከሆነው የዲሞክራሲ አስተምህሮት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመኾኑ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን በመግለፅ፣ ወኪሎቻቸውን በመምረጥ፣ ውሳኔዎችን በመስጠት ብሎም በሂደቱ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው እንዳስቻለ መዛግብትም ያስረዳሉ፡፡
በዚሁ አግባብ በምክክር ሂደቶች ሲሳተፉ የቆዩ የባለድርሻ አካላት ወኪሎችም ከላይ የተጠቀሱትን ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በአግባቡ ተግብረዋል። ይህም ዲሞክራሲን እንደ ባሕል ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል፡፡
4. የመነጋገር ባሕልን ማጎልበት
የአጀንዳ ማሰባሰብ በተከናወነባቸው የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ግጭቶችን ሀገር በቀል በሆኑ መንገዶች መፍታት የተለመደ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በሀገር በቀል የሽምግልና ስርዓት ያልተፈቱ የሀሳብ ልዩነቶችን ለመፍታት ሂደቱ ሀሳቦች በሚገባ እንዲንሸራሸሩ መንገዱን አመቻችቷል፡፡ ይህም የሀሳብ ልዩነት ያላቸው የተለያዩ ጎራዎች በሀሳብ ልዩነቶቻቸው ላይ ተወያይተው የመነጋገርን ባሕል እንዲያጎለብቱ አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!