ሕገ ወጥ ሼዶችን ሕጋዊ መስመርን እንዲከተሉ ማድረግ መቻሉን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

19

ደብረ ማርቆስ: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከ200 በላይ ሕገ ወጥ ሼዶችን ሕጋዊ መስመርን እንዲከተሉ ማድረግ መቻሉን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አገልግሎት አቅርቦት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አገልግሎት አቅርቦት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት በበጀት ዓመቱ ከመደበኛው የገቢ ግብር አሰባሰብ ተግባራት በተጨማሪ ከተማ አሥተዳደሩ ከሚያሥተዳድራቸው ሼዶች እና የተለያዩ አገልግሎቶች ተጨማሪ ገቢ እያስገኘ ነው፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የአገልግሎት አቅርቦት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስናቀ ሁነኛው ከ2 ሺህ 800 በላይ ከሆኑ ደንበኞች የአገልግሎት ኪራይ እየሰበሰቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የደንበኞችን እንግልት ለመቀነስ እና አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ ተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞቹን በማሠማራት ገቢ እየሰበሰበ ነው ብለዋል።

ከደንበኞች የሚሰበሰብ ውዝፍ ክፍያን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ተችሏል ያሉት ኀላፊው በበጀት ዓመቱ የአገልግሎት ኪራይን ጨምሮ ከሊዝ ጨረታ ሰነድ ሽያጭ በድምሩ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ሕገ ወጥነትን ለመከላከል እና ከፍትሃዊነት አንጻር የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት ኀላፊው። ከ2 መቶ በላይ ሕገ ወጥ ሼዶች ሕጋዊ መስመርን እንዲከተሉ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል፡፡

ከእሁድ ገበያ ተገቢውን ገቢ ለመሰብሰብ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በተያያዘም ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር እና እሁድ ገበያን መልክ ለማስያዝ ጥረቶች ቀጥለዋል ነው ያሉት፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በስኬት መጠናቀቁን የጸጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል አስታወቀ።
Next articleከ169 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።