
ባሕር ዳር: የካቲት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
38ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ። ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት ሀገራችን ኢትዮጵያም እንደ ኅብረቱ መቀመጫ ሀገር የሚጠበቅባትን አከናውናለች። አቀባበሉ፣ መስተንግዶው እና መርሐ ግብሮቹ እንግዶቻችንን ያስደመሙ ነበሩ ብለዋል።
እንግዶቿ የማይረሳ ትውስታ እና የማያረጅ ትዝታ እንዲኖራቸው አድርጋለች። በዚህ የተነሣ የቆይታ ጊዜያቸውን ያራዘሙ እንግዶች ብዙ ናቸው። ኢትዮጵያ ለኅብረቱ ዓላማዎች እና መርኾች መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት በጉባኤው ዝግጅት እና መስተንግዶ በተግባር አሳይታለች።
የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ብዙዎች የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። አዘጋጅ ኮሚቴው፣ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማቶች፣ የፕሮቶኮል ባለሞያዎች፣ የቴሌ እና የመብራት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የጸጥታ ተቋማት፣ የትራፊክ ፖሊሶች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብ እና የሰርከስ አባላት፣ ሆቴሎች፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሞያዎች፣ የጽዳት ባለሞያዎች፣ እንደ አንድ ልብ ሰሚ፣ እንደ አንድ አካል ፈጻሚ ኾነው ሠርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ለእንግዶቹ ተገቢውን ክብር እና መስተንግዶ በመስጠት፣ መንገዶች ሲዘጉ በትዕግሥት በመጠባበቅ፣ ለጉባኤው ስኬት የሚጠበቅበትን ሁሉ አድርጓል። ለሁላችሁም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ።
ሁላችንም በሀገር ፍቅር ስሜት፣ በሥርዓት እና በዲሲፕሊን በመሥራታችን እንግዶቻችንን አስደምመናል። የሀገራችንን ከፍታ አሳይተናል። ከ1 ሺህ በላይ የሚኾኑት የሚዲያ ሰዎች መልካም ገጽታችንን ለዓለም አሳይተዋል። ከ10 ሺህዎች የሚልቁት እንግዶች እየበለጸገች ስለምትገኘው ሀገራችን ምስክሮች ኾነዋል።
ይህ ትብብራችን እና ለሀገራችን ስኬት ያለን ቁርጠኝነት፣ ከጉባኤው በኋላም እንደሚቀጥል አምናለሁ።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት መኾኗ በዓለት ላይ እስኪጻፍ ድረስ ጥረታችን ይቀጥላል። በድጋሜ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!