
ደብረ ብርሃን: የካቲት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል።
የውኃ ማጠራቀሚያ ማዕከል ጨምሮ የዝርጋታ እና ሌሎች ሥራዎች ተከናውነዋል።
በከተማው እቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ ልቼ ቀበሌ አሥተዳደር ላይ ከመንግሥት በጀት ውጭ በማኀበረሰቡ ተሳትፎ የተገነቡ የመንገድ ግንባታ፣ የኤሌክትሪክ ኀይል መስመር ዝርጋታ እና የንጹህ መጠጥ ውኃን ጨምሮ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የተገነቡ ቤቶች ተጠናቀው ተመርቀዋል።
በፕሮጀክቶች ምርቃት ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በደብረ ብርሃን ከተማ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ማኅበረሰቡን በማሳተፋቸው ውጤታማ ኾነዋል ብለዋል።
በከተማዋ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለምረቃ በቅተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ማኅበረሰቡን ተሳታፊ አድርጎ መሥራት ውስን የኾነውን በጀት በአግባቡ እንድንጠቀም አድርጓል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡም በእኔነት ስሜት ተቋማቱን እንዲንከባከብ ያደርጋል ብለዋል።
ለምረቃ የበቁት እነኝህ ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት አውታሮች ተጠብቀው ለረዥም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን