
ጎንደር: የካቲት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛ ዙር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቃል ኪዳን ቤተሰብ ትውውቅ እና ትስስር መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
ከተጀመረ 6ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮግራም ተማሪዎች ከቤተሰብ የመራቅ ስሜት እንዳይሰማቸው በከተማዋ ነዋሪ ከኾኑ ግለሰቦች ጋር በማገናኘት በርካታ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው።
ባለፉት አምስት ዓመታት ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡ ከሦስት ሺህ በላይ ተማሪዎች እያንዳንዳቸው እንደ ወላጅ እና አሳዳጊ የሚንከባከቧቸውን ቤተሰብ ማፍራት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡
ፕሮጀክቱ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ አዲስ ተማሪዎች የጎንደር እና አካባቢውን ማኅብረሰብ ባሕል፣ እምነት እና እሴቶችን አውቀው ከማኅብረሰቡ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዲፈጥሩ ያስቻለ መኾኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ.ር) ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ በመሠረቷቸው ቤተሰባዊ ግንኙነት መሠረት በበዓል ወቅት አብሮ የማሳለፍ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲያጋጥማቸውም እንደ ወላጅና ልጅ በቅርብ እየተገናኙ በመመካከር በጋራ የመፍታት ባሕላዊ እሴቶች ማዳበራቸውን በፕሮጀክቱ ታቅፈው የቆዩ ተማሪዎች ተናግረዋል።
በቤተሰብ ፕሮጀክቱ ተማሪዎችን ተቀብለው እንደ ወላጅ ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠርና በመንከባከብ ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን በመወጣት እስከ ምርቃታቸው ድረስ ጥሩ ግንኙነት መመሥረታቸውን ዶክተር አራጋው እሸቴ እና ዶክተር አያሌው ተመስገን ነግረውናል።
የቃል ኪዳን ቤተሰብ ኘሮግራሙ የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚያጠናክር ተግባር መኾኑን ልጆቻቸው በቃል ኪዳን ፕሮግራሙ የታቀፉላቸው ወላጆች ገልጸዋል።
በቀጣይም ይህን ተግባር በማስፋት ሁሉም አካባቢዎች ላይ የቃል ኪዳን ትስስር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ነው ወላጆቹ የተናገሩት።
ዘጋቢ:- ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን