ዩኒዶ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

29

ባሕር ዳር: የካቲት 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከ38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የዓለም አቀፍ አጋርነት እና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ፋቱ ሀይዳር ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ምስጋኑ በብሔራዊ የኢንዱስትሪ ልማት እየተተገበሩ በሚገኙ ፕሮጀክቶች ማለትም በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በግብርናና ምግብ ማቀነባበሪያ ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

ለዚህ ሥራ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ድጋፍ አስፈላጊ እንደኾነ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ኢትዮጵያ እና ዩኒዶ በቴክኒክ ድጋፍ፣ በአቅም ግንባታ፣ በልምድ እና በቴክኖሎጂ ልውውጥ ላይ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ምክክር ተደርጓል።

ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ፋቱ ሀይዳር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከወራት በፊት የተካሄደውን ከረሃብ ነጻ ዓለም ኮንፈረንስ በተሳካ መንገድ በማስተናገዷ አመስግነው ድርጅታቸው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የታደሰ አጋርነት ወጥ የሆኾ ክትትልን ይፈልጋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየቃል ኪዳን ቤተሰብ ኘሮግራሙ የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚያጠናክር ነው።