ደብረ ብርሃን: የካቲት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ያለውን የውኃ ሀብት እና የሚሰጠውን አገልግሎት በዕውቀት፣ በቴክኖሎጂ እና በቅንጅት መምራት ተቀዳሚ ተግብር ሊኾን እንደሚገባው ተጠቁሟል።
የአማራ ክልል ከተሞች የመጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤቶች ማኅበር 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በደብረብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው።
በዚህ መርሐግብር ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) “በኢትዮጵያ ያለውን የውኃ ሀብት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አመራርን በመተግበር ማሥተዳደር ይገባል” ብለዋል።
በክልሉ የውኃ አገልግሎት ማኅበር ተቋቁሞ መሠራቱ ትልቅ ልምድ ሰለኾነ ለሌሎች ተሞክሮ የሚኾን ሥራ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር ) የውኃ ሀብቱን በፍትሐዊነት ተደራሽ ለማድረግ የቴክኖሎጅ፣ የዕውቀት እና የክህሎት አቅምን በፋይናንስ አጠናክሮ መምራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ጉዳይ የሁሉም የጋራ ፍላጎት በመኾኑ በሚገነቡ የውኃ ተቋማት ላይ የጋራ ጥበቃ በማድረግ በኩል የሚታየውን ክፍተት መሙላት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የካቲት 9/2017 ዓ.ም በከተማው የተሠሩ የውኃ ፕሮጀክቶች የጉብኝት እና ምረቃ መርሐግብር ይከናወናል ተብሎም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ አበበች የኋላሸት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!