
ባሕር ዳር፡ የካቲት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያን እና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሃሳብ በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡ በጉባኤው የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኀላፊዎች እና እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በ38ኛው የኅብረቱ ጉባኤ ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና የማግኘት ጥያቄ የክፍለ ዘመኑ ፍትሐዊ ጥያቄ ነው” ብለዋል፡፡ የአፍሪካ ፍትሐዊ የውክልና ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል፡፡
አፍሪካ ትኩረት ልትሰጣቸው የሚገቡ በርካታ ችግሮች ያሉባት አሕጉር ናት ያሉት ዋና ጸሐፊው የሰላም እና ደኅንነት ጉዳይ ቀዳሚው መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሱዳን እንዳልነበረች ስትኾን በዐይናችን እያየን ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው በመሳሪያ እና በኀይል የሚመለስ ጥያቄ ስለማይኖር ለውይይት እና ለንግግር መቀመጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ተመሳሳይ ችግሮች በኮንጎ፣ በሶማሊያ እና ሌሎች ሀገራትም እየታየ ነው፤ አፍሪካ የሰላም እና ደኅንነት ችግሮችን ቅድሚያ ሰጥታ መፍታት ይኖርባታል ነው ያሉት፡፡
ሌላው የአፍሪካ የትኩረት መስክ የአየር ንብረት ለውጥ ሊኾን እንደሚገባ ዋና ጸሐፊው ጠቁመዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በሚፈጠር የተፈጥሮ አደጋ በርካታ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በጎርፍ፣ ድርቅ እና ረሀብ እየተፈተኑ ነው ብለዋል፡፡ ችግሩ የአህጉሪቷን ጥረት ብቻ ሳይኾን ያደጉ ሀገራትን ተሳትፎም ስለሚጠይቅ በትብብር መሥራት ይጠይቃል ብለዋል። አፍሪካውያን ባልፈጠሩት ችግር እየተፈተኑ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!