
ባሕር ዳር፡ የካቲት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 38ኛ ው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ “የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሃሳብ በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡ በጉባኤው የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኀላፊዎች እና እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ መክፈቻ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በነጻነት ተምሳሌቷ፣ በአፍሪካ ኅብረት መሥራቿ እና አመቻቿ መዲናችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ ስል እንደ ትናንቱ ብቻችን ቆመን ሳይኾን እንደ አኅጉር በጋራ ቆመን በመኾኑ የተሰማኝን ደስታ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የአፍሪካ የማካካሻ ጥያቄ ችሮታ ወይም የፋይናንስ ድጋፍ ሳይኾን የፍትህ ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል፡፡ “አፍሪካ ሙሉ አቅሟን እንድትጠቀም አንድነት እንጂ መከፋፈል አይገባትም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሕጉሪቷ ዛሬም በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዳሏት አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ጥያቄ ፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን የህልውናም ጭምር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሕጉሪቱ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ ቀጣናዊ ውጥረቶችን መፍታት፣ ታሪካዊ ክፍፍሎችን ማስወገድ እና በአንድነት እሳቤ መነሳት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሞዴል የሚኾን የመደመር እና የመሰባሰብ እሳቤን እየተገበረች መኾኗንም አንስተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!