ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ፋይሌመን ያንግ ጋር ተወያዩ።

21

ባሕር ዳር፡ የካቲት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ፋይሌመን ያንግን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ ትላንትና ዛሬ ከተባበሩት መንግሥታት አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድርጋቸውን ጠቅሰዋል።

ከተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያና የመንግሥታቱ ድርጅት የረጅም ዘመን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ሀገራዊ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንና መግባባት ላይ መድረሳቸውን አንስተዋል።

በተመሳሳይ ዛሬ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ፋይሌመን ያንግ ጋር የጠቅላላ ጉባኤው ስልጣንና ተግባር እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ በነበረው የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፎርም ላይ ያተኮረ እንደነበር ጠቅሰዋል።

በተለይም አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ተገቢውን ውክልና በምታገኝበት ጉዳይ ላይ ጠቃሚ ሀሳቦች መለዋወጣቸውን ገልጸዋል።

የቀድሞ የካሜሮን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ፋይሌመን ያንግ በበኩላቸው፥ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በነበራቸው ውይይት የተባበሩት መንግሥታትን እና አፍሪካን በተመለከተ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቁልፍ የሆነች ሀገር ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ በተመድ ቻርተር በጽኑ የምታመን ወሳኝ አባል ሀገር መሆኗንም ገልጸዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው ኢትዮጵያና የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፥ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

Previous articleኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መሠረት።
Next articleየመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን አስመረቀ።