ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መሠረት።

24

ባሕር ዳር: የካቲት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የአፍሪካውያን የነፃነት አርማ እና የጥቁር ሕዝቦች የተስፋ ምንጭ ኾና ቆይታለች። ለአፍሪካዊያን ነፃነት መጠበቅ በየመድረኩ ተሟግታለች።

ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች ሀገሮች መካከል አንዷ እንደመኾኗ አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንድትኾን ያልተቆጠበ ተጋድሎ አድርጋለች፡፡ ለአፍሪካ ሕዝቦች ዕድገት እና ልማት የበኩሏን አስተዋፅኦ የማድረጓን ያህል ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረትም ግንባር ቀደም ያደርጋታል።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የምሥረታ ሂደት፦
የአፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በወርሃ ግንቦት በ1955 በአዲስ አበባ ተገናኙ። የሚኒስትሮች ኀላፊነት ደግሞ የድርጅቱንም የወደፊት ቻርተር ለመቅረጽ ነበር፡፡

በሚኒስትሮች መሥራች ጉባኤ በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ከተማ ይፍሩ ሊቀመንበር ኾነው ተመረጡ። በጉባኤው ላይም ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ እና ጋና ቻርተር በመቅረጽ ለውይይት አቀረቡ፡፡

በጋና የቀረበው ቻርተር የካዛብላንካውን ቡድን አቋም ሲያንፀባርቅ፣ በናይጄሪያ በኩል የቀረበው ቻርተር የሞኖሮቪያውን ቡድን አቋም ያንጸባረቀ ኾነ። በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ቻርተር ግን ሁለቱንም የሚያስታርቅ እና የሚያግባባ ነበር።

በወቅቱ ኢትዮጵያ ያቀረበችው የረቂቅ አጀንዳ ነጥቦች ቻርተር እና ቋሚ ጸሐፊ ያለው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና ቀዳሚ መሥሪያ ቤት መመሥረት፣ በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ደኅንነት፣ በትምህርት እና ባሕል፣ ቅኝ ግዛትን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ፣ የዘር አድልኦ እና አፓርታይድን በመዋጋት የዘር ልዩነት እንዲወገድ ማመቻቸት፣ አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ማኅበራት የሚቋቋሙበትን መንገድ ማመቻቸት እና የጦር መሣሪያ ቅነሳ እንዲደረግ የሚሉት ናቸው። ኢትዮጵያ ያቀረበችው ቻርተርም ለውይይቱ ይበልጥ ተመራጭ መኾኑን ኤርሚያስ ጉልላት “ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና ፓን አፍሪካኒዝም” በሚል በ2009 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ ገልጸውታል።
ለዚህ ታላቅ ሀሳብ ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ እና የታላቋ ሀገር መሪ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኀይለ ሥላሴ በግንባር ቀደምትነት ይነሳሉ። አፍሪካውያን ተሰባስበው የራሳቸውን እድል በራሳቸው እንዲወስኑ፣ ነጻነታቸውን እንዲያስከብሩ፣ ሉዓላዊነታቸውን እንዲያጸኑ መሠረቱን ጥለዋል። ድርጅቱንም ግንብተዋልና።

የአፍሪካውያንን ጥቅም ለማረጋገጥ የካዛብላንካ እና የሞኖሮቪያ ቡድኖችን ወደ አንድ ለማምጣት ለአፍሪካ መሪዎች ጥሪ ቀረበ። 32 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በአዲስ አበባ ተሰባሰቡ። የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመፍጠር እና በእግሩ እንዲቆም ከፍተኛ ትግል ተደረገ። ለቀናት ውይይት ከተደረገ በኋላ መሪዎቹ ግንቦት 1955 ዓ.ም በ33 አንቀጽ የተዋቀረውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተርን መሠረቱ፡፡ ቻርተሩም በአማርኛ፣ በአረበኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ የድርጅቱ ምስረታ ይፋ ኾነ። ድርጅቱ ከተመሠረተ ጀምሮ ለጥቁሮች መብት ታገለ። የቀሩ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ እንዲወጡ የበኩሉን ሲያበረክት ቆይቷል።
ድርጅቱ በ1995 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ደርባን ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲዋቀር ተደረገ። ኅብረቱ በጠንካራ መሠረት ላይ መቆሙን አባል ሀገራቱ በወቅቱ አረጋገጡ። ተዳክሞ የነበረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ መልክ መጠናከሩን ተገለጸ።
የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ከ62 ዓመታት በኋላ 38ኛውን የመሪዎች ጉባኤ ለማካሄድ የድርጅቱ መጠንሰሻ በኾነችው አዲስ አበባ ዛሬም ተሰባስበዋል። ጉባኤው ዛሬ እና ነገ የሚካሄድ ሲኾን በተለያዩ አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎም ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

Previous articleየአፍሪካ ሕዝቦች ኩራት፡ ኢትዮጵያ
Next articleፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ፋይሌመን ያንግ ጋር ተወያዩ።