የአፍሪካ ሕዝቦች ኩራት፡ ኢትዮጵያ

15

ባሕር ዳር: የካቲት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለዘመናት ነጻነቷን አስጠብቃ እና ታፍራ የኖረች ሀገር ናት። ከአፍሪካ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የመንግሥታቱ ማኅበር አባል የነበረች ብቸኛዋ ሀገርም ናት።
በየጊዜው አህጉሩን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት የሚነሱትን የውጭ ሀገራት ወራሪዎች አጥብቃ አውግዛለች። ሽንጧን ገትራ ታግላለች። ወራሪዎችን በፍትሕ አደባባይ አቁማ በመሞገትም ድል ነስታለች።
ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ ነጻ ሀገር ብትኾንም መላው የአፍሪካ ሀገራት ነጻ ሳይወጡ ነጻነቷ ሙሉ ስለማይኾን አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲኾኑ መሰዋዕትነት ከፍላለች። የየሀገራቱን የነጻነት ታጋዮች አሠልጥና ለነጻዋ አፍሪካ ምሥረታ ዘብ ቁማለች፡፡ ለዚህም የዚምባብዌው ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ እና የደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን ተጠቃሾች ናቸው።
ፍትሕ የማይሻው የምዕራባውያኑ ጎራ የኢትዮጵያን ጥረት ለማሰናከል ላይ ወጥቶ ታች ወርዶ ቢፍጨረጨርም የኢትዮጵያን ፍትሐዊ ትግል መግታት ግን አልቻለም። በኢትዮጵያ ተጋድሎም እስከ 1955 ድረስ 32 ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ኾነዋል፡፡
ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ የወጡት ሀገራትም በዋናነት በኢትዮጵያ አስተባባሪነት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መስርተዋል። ዓላማቸው ነጻነታቸውን ያላገኙ ሀገራት ነጻ እንዲኾኑ እና ነጻነታቸውን ያገኙት ደግሞ ነጻነታቸውን ሙሉ እንዲያደርጉ ነበር።
የአፍሪካ ሀገራትን አንድነት እና ኅብረት በማጎልበት፣ ለአፍሪካ ሕዝብ የተሻለ ሕይዎት ለማምጣት፣ ትብብር እና ጥረትን ማጠናከር ወሳኝ መኾኑን ኢትዮጵያ አስቀድማ አውቀዋለች። የአባል ሀገራትን ሉዓላዊነት እና የግዛት እንድነት ለመጠበቅ፣ ቅኝ ገዥዎችን ከአህጉሪቱ ማስወገድ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀፍ ውስጥ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲኖር ማድረግ እና የአባል ሀገራቱ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መኾኑን ኢትዮጵያ ተገንዝባለች። የትምህርት፣ ባሕል፣ ጤና፣ የደህንነት እና መከላከያ ፖሊሲዎችን ማቀላጠፍም እንደሚገባ እንዲሁ።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት እና ኅብረት ላይ ያላት አቋም በመሪዎቿ መቀያየር የማይናወጥ ኾኖም እነኾ ዛሬ ድረስ ዘልቋል። ኡትዮጵያ ከነጻነት ባሻገር የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ችግር ለመቅረፍ በግንባር ቀደምትነት የውስጥ አጀንዳ ቀርጻ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገችም ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔዎች ላይ የአፍሪካን አጀንዳ ይዛ በመሞገት ላይም ናት። ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር፣ የተፈጥሮ ሃብት እና ለዓለም ኢኮኖሚ የጎላ አበርክቶ ያላት አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና አለማግኘቷ ደግሞ ሌላው አህጉሪቷን ያሳሰባት ጥያቄ ኾኖ ዘልቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋም የኾነው የጸጥታው ምክር ቤት ሲመሠረት የተሳተፈችው ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር ኢትዮጵያ፤ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት እየሞገተች ትገኛለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጎተሬዝም በቅርቡ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት በኢትዮጵያ የቀረበውን ጥያቄ “ተገቢ እና ፍትሐዊ” ብለውታል።
አፍሪካ አሁንም ከግጭት፣ ከረሃብ፣ ከስደት እና ከሰቆቃ ባለመላቀቋ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞችን አሳስቧል። መሪዎቿን አሰባስባ እንድትመክር ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች።
የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኙ ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባ አፍሪካ የጋራ የመገበያያ ገንዘብ ሳይኖራት፣ ያለቪዛ ዜጎቿ በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ መዘዋወር ሳይችሉ፣ አፍሪካ የራሷን ዕድል በራሷ ለመወሰን ሳትበቃ፣ በምግብ ራሷን ሳትችል፣ የምዕራባውያን ሀገራት ምጽዋት ጠባቂ እስከኾነች ድረስ ነጻነቷን ተጎናጽፋለች ማለት አይቻልም ይላሉ። የኢትዮጵያ ሀሳብም እንዲሁ ነው። አፍሪካን የተሟላ ነጻነት ባለቤት ማድረግ።
ሌብነት፣ የሥልጣን ሽኩቻ፣ የሃብት ብዝበዛ እና ስደት የአፍሪካ መገለጫ እንደኾነ መቀጠል እንደሌለበት ኢትዮጵያን ያሳስባታል። በመኾኑም መሪዎች በመዲናቸው አዲስ አበባ ከትመው በመምከር መፍትሔ እንዲያመጡ ኢትዮጵያ ዛሬም እየሠራች ትገኛለች።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቅ ገብሬ ስሜነህ አፍሪካ ሌሎች እንደሚሉት ተስፋ ቢስ እና ጥቁር አህጉር ሳትኾን ወርቃማ አህጉር ናት ይላሉ።
የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ እንደሚሉት አህጉሪቷ ተፅዕኖ መፍጠር እንድትችል የራሷ የመገበያያ ገንዘብ እና ዜጎች ያለቪዛ ወደ ፈለጉት ሀገራት ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዲችሉ ኹኔታዎችን ማመቻቸት ይገባል። አፍሪካ ድምጿን የምታሰማበት እና ዜጎቿን የምታነቃበት የራሷ ሚዲያም ሊኖራት ወቅቱ ያስገድዳል ነው የሚሉት። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውክልና ሊኖራት ግድ ይላልም ይላሉ።
እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎች እንዲመለሱ፤ አህጉሪቷ በየዘመኑ ከሚፈጠሩ የውጭ ተፅዕኖዎች ነጻ ለመኾን ኢትዮጵያ አሁንም የራሷን ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገች እንደኾነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ለሚልቀው የአፍሪካ ሕዝብ ኩራትነቷም ዛሬም ቀጥላለች። 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያን እና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ መልዕክት በአዲስ አበባ ዛሬ እና ነገ ይካሄዳል። ጉባዔው በተለያዩ አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎም ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የግሎባል ፈንድ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ፒተር ሳንድስ ጋር ተወያዩ።
Next articleኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መሠረት።