“ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

36

ባሕር ዳር: የካቲት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ድጋፍ ማድረጓን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ። በኢትዮጵያ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በኢጋድ ቅንጅት የተዘጋጀ ለሱዳን ሕዝብ የሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ ላይ ያተኮረ ከፍተኛ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለሱዳን ሕዝብ ሰላም እና መረጋጋት በሁሉም መስክ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ብለዋል። ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሱዳን ሕዝብ ጎን ትቆማለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሏን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

በመድረኩ 14 ሚሊዮን ሱዳናውያንን ያፈናቀለው የእርስ በእርስ ግጭት በመባባሱ ከ30 ሚሊዮን በላይ የሀገሪቱ ዜጎች የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተጠቁሟል። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያ የ15 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የ200 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ አድርገዋል።

የተደረገው ዕርዳታ ተደራሽ እንዲኾን በተጨማሪም ለመጪው የረመዳን ፆም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ሀገራቱ መክረዋል። በመድረኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጨምሮ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህመት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከ291 ሚሊዮን ብር በላይ የጤና ልማት ሥራ ሥምምነት ተፈራረመ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከኬኒያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ጋር ተወያዩ።