የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከ291 ሚሊዮን ብር በላይ የጤና ልማት ሥራ ሥምምነት ተፈራረመ።

42

ባሕር ዳር: የካቲት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ ሪፕሮዳክቲቭ ቾይዝ ከተባለ በጤናው ዘርፍ ከሚሠራ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በጤና መድኅን አገልግሎት ድጋፍ ላይ ሥምምነት ተፈራርሟል። በተገኘው በ291 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጀት በ15 ዞኖች በ60 የጤና ተቋማት ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ነው።

የኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ሽብሩ ድርጅታቸው በጤናው ዘርፍ የታቀደውን የእናቶች እና ወጣቶች ሥነ ተዋልዶ ሥራ እያገዘ መኾኑንም ተናግረዋል። ድርጅቱ ሜሪ ስቶፕ በሚል መጠሪያ በአማራ ክልል በጤናው ዘርፍ ለዓመታት እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው ዛሬም በእናቶች፣ ሕጻናት እና የወጣቶችን የሥነ ተዋልዶ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር መሥራትን ለማስቀጠል መኾኑን ገልጸዋል።

የሥነ ተዋልዶ ጤና ያለውን ተፈላጊነት ጠቅሰው በተለይም ተደራሽነት በሌለባቸው አካባቢዎች እየተሠራ ነው ብለዋል። አሁንም ከተጠየቁት ድጋፍ ሰጭዎች መካከል ከጌትስ ፋውንዴሽን በተገኘው ድጋፍ በአማራ ክልል የሚደረገውን የጤና እንቅስቃሴ ለመደገፍ ተመድቧል ብለዋል።

ድርጅታቸው በጤናው ዘርፍ በውጭ ድጋፍ ብቻ መንጠልጠል ዋጋ እንደሚያስከፍል በመረዳት በበጎ አድራጎት እና የተገኘን ድጋፍ ዘላቂ አቅም የማድረግ ሞዴል እየተከተለ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም ከተረጂነት ወጥተው ራሳቸውን ችለው የሚሠሩባቸው ዘርፎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጋር ለመሥራት በመምጣቱ አመሥግነዋል። በኢትዮጵያ የመከላከል እና አክሞ ማዳን የጤና ፖሊሲን ለመተግበር የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ጥሩ ቢኾንም ራስን መቻል ዘላቂ መፍትሄ መኾኑን አንስተዋል።

ዘርፉ እርዳታ ሲቆም የሚቆም እንዳይኾን በራስ አቅም የመራመድን አስፈላጊነት አንስተዋል። ለዚህም ሁሉም ኀላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።

ኤም ኤስ አይ ባለፉት ዓመታት ለጤና ተደራሽነት እና ለፍትሐዊ አገልግሎት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው የጤና አገልግሎትን በዘላቂነት ለመሥራት እና ፕሮጀክቶችን በማፈላለግም ለጤና ተቋማት የሚያደርገውን ሁለገብ ድጋፍ አቶ አብዱልከሪም አድንቀዋል።

አሁን ላይ ካቀረባቸው ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ለችግረኞች የጤና መድኅን አገልግሎት ሽፋን ድጋፍ ማድረጉ የመንግሥትን ዘላቂ የጤና ፖሊሲ ውጤታማ ለማድረግ ከማገዙም በተጨማሪ ማኅበራዊ ኀላፊነትን መወጣት መኾኑን ገልጸዋል።

ኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በ60 የጤና ተቋማት የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ውሎ የሥራው ውጤታማነት ወደ ሌሎች በተሞክሮነት ማስፋት እንዲችል አደራ ብለዋል።

ከሥምምነት ፊርማው በተጨማሪም ኤም ኤስ አይ ኢትዮጵያ በክልሉ በጤናው ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት እና ውጤቶች ላይ ገለጻ ተደርጓል።

ድርጅቱ በባሕር ዳር፣ በደብረ ማርቆስ እና በደሴ ከተሞች ለሚኖሩ 130 አቅመ ደካሞች የጤና መድኅን አገልግሎት ሽፋን ለመስጠት ግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍም አድርጓል።

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሞሪሺየስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቪንቻንድራ ራምጎላም አዲስ አበባ ገቡ።
Next article“ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)