ምክር ቤቱ የቀረቡለትን ረቂቅ አዋጆች መርምሮ አጸደቀ።

104

ባሕር ዳር: የካቲት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ለአራተኛ ቀን ቀጥሏል። ምክር ቤቱ በአራተኛ ቀን የጉባኤ ውሎው የቀረቡለትን ረቂቅ አዋጆች እና ረቂቅ ደንብ መርምሮ አጽድቋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ረቂቅ አዋጆችን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል። ረቂቅ አዋጆቹ ፍርድ ቤቱ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች ስኬታማ እና ዘላቂ ለማድረግ፣ ዘመኑን እንዲዋጅ እና የዳኝነት ሥርዓቱን የተሳካ ለማድረግ ያስችላሉ ነው ያሉት።

የዳኝነት ሥርዓቱን ነጻ እና ገለልተኛ ለማድረግ፣ አዳዲስ እና አዳጊ ሃሳቦችን ለማስተናገድ እንደሚያስችልም አንስተዋል።

የዳኝነት ሥርዓቱን ነጻ እና ገለልተኛ ማድረግ ግድ እንደሚልም ተናግረዋል። የፍትሕ ሥርዓቱን ጠንካራ ለማድረግ እና የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ በባሕላዊ እሴቶች የመዳኘት ፍላጎት እና ልምድ እንዳለው ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ለባሕሉ ዕውቅና መስጠት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ጊዜን እና ወጭን እንደሚቆጥብ፣ የመደበኛ የዳኝነት ሥርዓቱን ሥራ እንደሚያቀል እና ዘላቂ ሰላምን እንደሚያሰፍንም ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ፍርድ ቤቱ የተቋም ግንባታውን ለማጠናከር እና የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች የተሳካ ለማድረግ እንደሚረዱት ተናግረዋል።

የቀረቡት ረቂቅ አዋጆች የነበረውን የሕግ ክፍተት የሚሞሉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት እንዲኖር ረቂቅ አዋጆቹ አስፈላጊ መኾናቸውን አንስተዋል።

የምክር ቤት አባላትም ረቂቅ አዋጆቹ አሳሪ ሕጎችን እንደሚያሻሽሉ ተናግረዋል። ረቂቅ አዋጆቹ ፍርድ ቤቱ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች ለማስቀጠል እንደሚያግዘውም ገልጸዋል። የዳኝነት ሥነ ምግባርን ማስተካከል እና ፍትሐዊ የኾነ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ምክር ቤቱ መርምሮ ያጸደቃቸው ረቂቅ አዋጆች:-

👉 የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ ረቂቅ አዋጅ፣

👉 የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና ዕውቅና ለመስጠት የወጣ ረቂቅ አዋጅ፣

👉 የአማራ ክልል ፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት እንደገና ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣

👉 የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ለመወሰን የወጣ ረቂቅ ደንብ ናቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ እና ቻይና በፍትሕ ዘርፍ በትብብር ለመሥራት ተስማሙ።
Next articleየሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ አዲስ አበባ ገቡ።