
ባሕር ዳር: የካቲት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እና ቻይና በፍትህ ዘርፍ በትብብር መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። የመግባቢያ ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የፍትህ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሐና አርአያስላሴ የፈረሙ ሲሆን በቻይና በኩል ደግሞ የህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ የፍትህ ሚኒስትር ሂ ሮንግ ፈርመዋል።
ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በፍትህ ዘርፍ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለማመቻቸት፣ በፎርንሲክ ምርመራ፣ በግልግል ዳኝነት፣ በነጻ የህግ ድጋፍ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
እንዲሁም የፍትህ ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ልውውጦችን ለማድረግ፣ ለባለሙያዎች የትምህርት ዕድል ለመፍጠርና በሁለቱ ሀገራት ፍትህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል የተቋማት ጥምረት በመፍጠር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ነውም ተብሏል፡፡
አሁን የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድም በሁለቱ ሀገራት ተቋማት መካከል ቀደም ሲል በፍትህ ዘርፍ የነበረውን ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ኢዜአ ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!