
ባሕር ዳር: የካቲት 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ለ38ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ሲሰባሰቡ ከሚቀርቡላቸው ጉዳዮች አንዱ ከቪዛ ነፃ እንቅስቃሴን እንዲተገብሩ የሚለው ነው። የአፍሪካ ኅብረት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የአሕጉሪቱ መንግሥታት ለቀጣናዊ ውህደት፣ ለእርስ በርስ ንግድ እና ለምጣኔ ሃብት ዕድገት ፈተና የኾነውን የቪዛ ገደብ እንዲያስቀሩ ጠይቀዋል።
የኅብረቱ የሥራ ኀላፊዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች እና የንግድ መሪዎች የነፃ ቪዛ ትግበራን ማፋጠን በሚል በተዘጋጀ ስትራቴጂካዊ ውይይት ላይ የቪዛ ገደብ እና ቀጣናዊ ውህደት አብረው የማይሔዱ ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል። የአፍሪካ ኅብረት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽነር አምባሳደር አልበርት ሙዴንዳ ሙቻንጋ አፍሪካውያን በአሕጉራቸው በነፃ መንቀሳቀስ ካልቻሉ ስለ አፍሪካ ውህደት መናገር አንችልም ሲሉ ተናግረዋል።
የቪዛ ገደብ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የእርስ በርስ ንግድ እንዳያድግ ዋና እንቅፋት መኾኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል። ምንም እንኳ የኅብረቱ በነፃ የመንቀሳቀስ ፖሊሲ እና የአጀንዳ 2063 ድንበር አልባ አፍሪካን የመፍጠር ራዕይ ቢኖርም የነፃ ቪዛ እንቅስቃሴ ትግበራ ግን ዕድገቱ አዝጋሚ ነው።
ሩዋንዳ፣ ጋምቢያ፣ ሲሸልስ፣ ቤኒን እና ጋና ካለ ቪዛ እንቅስቃሴን ሲፈቅዱ ቀሪ ሀገራት ግን የቪዛ ገደብን ማስቀረት አልቻሉም።
“የተዋሃደች አፍሪካ በዕድል አትፈጠርም” የሚሉት የአፍሪካ ልማት ባንክ የቀጣናዊ ልማት፣ ውህደት እና የንግድ አቅርቦት ምክትል ፕሬዚዳንት ኔና ንዋቡፎ፣ የቪዛ ገደቦችን የሚያስቀር ደፋር አመራር እና የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ። የቪዛ ገደቦች ተንቀሳቅሶ መሥራትን፣ ንግድን፣ የፈጠራ ክህሎትን እና ልማትን ያዳክማሉ።
የሩዋንዳ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ፕሩደንስ ሴባሂዚ በነፃ ንግድ ቀጣና /AFCFTA/ በእውነት የምናምን ከሆነ የነፃ ቪዛ እንቅስቃሴ ለትግበራው የጀርባ አጥንት ነው ሲሉ ይናገራሉ። የአፍሪካ ኅብረት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የ2025 የነፃ ቪዛ ዘመቻ አስጀምረዋል። በዚህ ዘመቻ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የንግድ ሰዎች እና የሲቪል ማኅበረሰቦች በአህጉሪቱ ካለ ቪዛ እንቅስቃሴ ዕቅድ ትግበራ እንዲፋጠን ጥረት ያደርጉበታል ተብሏል።
በዘመቻው ነፃ ቪዛ እንቅስቃሴ ያስገኛቸው ስኬቶች፣ ለምጣኔ ሀብት ያለው ጠቀሜታ እና የጉዞ ገደቦችን ለማስቀረት ያለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚቀርብበትም ተጠቁሟል። የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችም በ38ኛው የኅብረቱ ጉባኤ የነፃ ቪዛ እንቅስቃሴ ትግበራን በተመለከተ ጠንካራ ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ይጠበቃል።
የአፍሪካ ኅብረት ጥሪም ግልፅ ነው፣ ሕዝቡ ይንቀሳቀስ፤ አፍሪካም ትበለጽጋለች።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!