‘‘ለሕገ ወጥ የሰዎች ደላላ ምንም ዓይነት ምሕረት አያስፈልግም፤ ይህ አገርን እንደማጥቃት ይቆጠራል።” ዶክተር ስዩም መስፍን

280

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከፌዴራል እና ከክልል የተወጣጣ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል በምዕራብ ጎንደር ዞን ከሱዳን ተመልሰው በአስገድዶ ለይቶ ማቆያ ቦታዎችን ጉብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ከምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ጋር ባጋጠሟቸው ችግሮች እና መፍትሔዎች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
ከፌፌራል እየተደረገ ያለው ድጋፍ አነስተኛ መሆንና ዞኑ ከሱዳን አጎራባች ነው፤ በሱዳን እየተስፋፋ የመጣው ወረርሽኝ ስርጭት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ደግሞ በአካባቢው የሚስተዋለው የሰዎች እንቅስቃሴ ከዞኑም አልፎ ለሀገሪቱ ስጋት መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።

በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ናሙና ወደ ጎንደር እና ባሕር ዳር እየተላከ ምርመራ እየተደረገ ቢሆንም ካለው ችግር አንጻር በዞኑ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ እንዲኖርም ጥያቄ ቀርቧል።

በቫይረሱ ተጠርጥረው ወደ ማቆያ ቦታዎች ለሚገቡ ሰዎች ማጓጓዥ ቋሚ መኪና ባለመኖሩ ለንክኪ ተጋላጭነት በመኖሩ በቋሚናት መኪና እንዲመቻችም ጥያቄ ቀርቧል።

እስከ ዛሬ 37 ሰዎች ከአስገድዶ ለይቶ ማቆያ ጠፍተዋል፡፡ ሰዎች ከለይቶ ማቆያዎች እንዳይጠፉ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት እንዳለበት እና ማቆያ ጣቢያዎች ኃላፊነት ወስደው መሥራት እንዳለባቸው ደግሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ስዩም መስፍን (ዶክተር) አሳስበዋል።
‘‘በእያንዳንዱ የድንበር ቦታ ላይ የፀጥታ አካል ማቆም ከባድ ነው’’ ያሉት ዶከተር ስዩም ምን ያክል የፀጥታ አካል እንደሚያስፈልግ መረጃው እንዲጠናከርና የአካባቢው ሚሊሻ፣ ልዩ ኃይል እና መከላከያ በጋራ እንዲሰማሩ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

የመኪና ችግሩ እንዲፈታ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ጋር በመነጋገር አንድ መኪና እንዲመድብላቸው ጥያቄ እንደሚቀርብም ተገልጿል።

ከክልሉ የማቆያ ቦታዎች እንዲገነቡ ጥያቄ መቅረቡን ዶክተር ስዩም አስታውሰው በጊዚያዊነት በቆርቆሮ የሚሰሩበት አማራጭ እንዲኖር ድጋፍ እንደሚደረግም አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡- ዳንኤል ወርቄ

Previous articleየዓለም ጤና ድርጅት ያልተረጋገጡ መድኃኒቶችን መጠቀም እንደማይገባ አስጠነቀቀ፡፡
Next articleየውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክና ከታማሚ ጋር ንክኪ የሌላቸው 19 ሰዎችን ጨምሮ በ25 ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ተገኘ፡፡