“የምሥራቅ አማራ ሥፍራዎች እና አጎራባች አካባቢዎች በበልግ ወቅት መደበኛ የዝናብ ሥርጭት ይኖራቸዋል”-የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል

51

ባሕር ዳር: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል በዓለም አቀፍ የጣቢያዎች ምልከታ ትስስር ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ፈጠራ እና የበልግ 2017 ዓ.ም ወቅታዊ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር ሲሳይ ቀለሙ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የአየር ሁኔታ ትንበያ ወሳኝነት አለው ብለዋል።

ሀገሪቱ ግብርና መር አሠራርን ስለምትከተል ተዓማኒ የቅድመ የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃ መስጠት አርሶ አደሩን ምርታማ እንዲኾን ከፍተኛ እገዛ ያደርገዋል ነው ያሉት።

ኢንስቲትዩቱ ዘላቂ እና ወጥ የአየር ንብረት ቅድመ ትንበያ እና ማስጠንቀቂያ መረጃ በትስስር ለመስጠት የሚያስችሉ የጎንደር፣ ባሕር ዳር እና ደብረ ማረቆስ ጣቢያዎች ደረጃ ይሻሻላል። ማንኩሽ ላይ ደግሞ አዲስ ጣቢያ ይቋቋማል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል የሚቲዎሮሎጂ ሳይንስ ተመራማሪ እንደግ አንለይ የ2017 የበልግ ወቅት ከየካቲት እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ይሸፍናል ብለዋል።

በኢንስቲትዩት በተሠራው የአየር ትንበያ ትንተና መሠረትም የበልግ ወቅት ዝናብን የሚጨምረው እና የሚቀነሰው የመካከለኛው እንዲሁም የፓስፊክ ውቅያኖስ አሁን ላይ በጣም እየቀዘቀዘ ነው ብለዋል።

የሕንድ ውቅያኖስ የሙቀት መጠን የተረጋጋ እና መደበኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት ተመራማሪው ይህም በበልግ ወቅት ዝናብ እንዲኖር የማድረግ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል ።

በ2017 የበልግ ወቅት አብዛኛው የምሥራቅ አማራ ሥፍራዎች እና አጎራባች አካባቢዎች፣ የደቡብ ጎንደር እና የምሥራቅ ጎጃም ወረዳዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በታች የኾነ የዝናብ ሥርጭት እንደሚኖርም አቶ እንደግ ገልጸዋል።

ይህን የዝናብ ስርጭት አርሶ አደሮች በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ተመራማሪው ጠቁመዋል።

በምዕራብ አማራ አልፎ አልፎ ዝናብ ይኖራል ነው ያሉት ተመራማሪው ። በፀሐይ የታገዘ ደመና እንደሚኖርም የጠቆሙት ተመራማሪው ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚከሰትም ተናግረዋል። ከዝናብ የሚገኘውን ውኃም አርሶ አደሩ በማቆር ለልማት እንዲጠቀምበት አቶ እንደግ መክረዋል።

በክልሉ በዝቅተኛ እና በቆላማ አካባቢዎች የቀኑ ሙቀት በጣም ይጨምራል ያሉት ተመራማሪው ወበቅ እና ምቾት የሚነሳ አየር ሁኔታ ይኖራል። በመኾኑም መረጃዎችን በመከታተል ኀብረተሰቡ አኗኗሩን ማስተካከል እንደሚገባው ተመራማሪው ለአሚኮ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍኖተ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሠራ ነው።
Next articleየአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የቀረቡለትን ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጸደ።