የፍኖተ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሠራ ነው።

31

ፍኖተ ሰላም: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ1954 ዓ.ም እንደተመሠረተ የሚነገረው የፍኖተ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል ካስቆጠረው ረጅም ዕድሜ አንፃር በሚፈለገው ልክ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት አለመስጠቱ በተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።

በሆስፒታሉ ውሰጥ ያገኘናቸው ተገልጋዮች ከዚህ በፊት በርካታ ችግሮች በመኖራቸው ለእንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸውን አንስተው አሁን ግን የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አድንቀዋል።

ይሁን እንጅ በሆስፒታሉ የሰው ኃይል እጥረቱን በማሟላት አገልግሎት አሰጣጡን ማሳለጥ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

ሆስፒታሉ ይስተዋሉበት የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ እና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መኾናቸውን የፍኖተ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ደጀኑ በላይ ተናግረዋል።

ከ6 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ ወጭ ሆስፒታሉን ለተገልጋዮች ምቹ እና ማራኪ ለማድረግ መሠራቱንም ገልጸዋል።

የተጀመረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ለማድረግ የግብዓት እና የጤና ባለሙያ እጥረቶችን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን ነው አቶ ደጀኑ የተናገሩት ።

በዞኑ አምስት ሆስፒታሎች እና 51 ጤና ጣቢዎች መኖራቸውን ያነሱት የምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ኤፍሬም ክፍሌ የጤና ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ማኅበረሰቡን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በተለይም የጤና ተቋማትን ጽዱ እና ማራኪ ለማድረግ የፍኖተ ሰላም ከተማን ጠቅላላ ሆስፒታል ተሞክሮ በማስፋት መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል።

የግብዓት ችግሮችን ለመቅረፍ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና አጋር አካላት ጋር በመኾን ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል።

Previous article“በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን በአካባቢ ልማት እና በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ በማሳተፍ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል” የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ
Next article“የምሥራቅ አማራ ሥፍራዎች እና አጎራባች አካባቢዎች በበልግ ወቅት መደበኛ የዝናብ ሥርጭት ይኖራቸዋል”-የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል