
ደሴ: የካቲት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ያለፉት ሦስት ዓመታት የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ ፕሮጀክት አፈጻጸም ማጠቃለያ እና የ2017 ዓ.ም አዲስ ተጠቃሚዎችን የማስጀመሪያ መርሐግብር በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል፡፡
የሰቆጣ ከተማ ምግብ ዋስትና እና ልማታዊ ሴፍቲኔት ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ዘሩ ጌታወይ በከተማው በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከ2 ሺህ 600 በላይ ወገኖችን የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙትን የመለየት፣ የመስሪያ ቦታ የማጣራት እና የማስፈቀድ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀድያ መሐመድ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡
በዚህም በከተማ ግብርና፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እና በሌሎችም መርሐግብሮች የታቀፉ ወገኖችን በማሳተፍ በምግብ ራሳቸውን ችለው ምርት ለገበያ ጭምር እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የነበሩ ከ4ሺህ 600 የሚበልጡ ተጠቃሚዎችን በዘላቂነት በማቋቋም የተመረቁ ሲኾን ከ27 ሺህ የሚበልጡ ወገኖችን ደግሞ በአዲስ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራ አሥኪያጅ ተሻገር አዳሙ በከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐግብር ከ20 ሺህ የሚበልጡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን በአዲስ ተጠቃሚ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት እና ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሐሰን ሙህዬ “በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን በአካባቢ ልማት እና በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ በማሳተፍ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል” ብለዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውሰው ዘንድሮ ብቻ ከ10ሺህ የሚበልጡ ወገኖችን በዘላቂነት በማቋቋም እንዲመረቁ እና ከመርሐግብሩ እንዲወጡ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት ደግሞ በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ከ116ሺህ የሚበልጡ ወገኖችን የመርሐግብሩ ተጠቃሚ ለማድረግ የልየታ፣ የማጣራት እና የሌሎችም ቅደመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ መርሐግብር የዜጎችን የሥራ ባሕል በማሻሻል፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የቁጠባ ባሕልን በማሳደግ እና የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማጠናከር ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ ፦አንተነህ ፀጋዬ